<<ለሀገራዊ ምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የመለየት ስራ በቅርቡ ይጀመራል፡፡>>

12/04/2016

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዛሬው ዕለት በፅህፈት ቤቱ በሰጠዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ በ327 ወረዳዎች በሀገራዊ ምክክሩ መነሳት አለባቸው ያሏቸውን አጀንዳዎች የሚለዩ ተሳታፊዎች መለየታቸውን አስታውቋል።

ከትግራይና ከአማራ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች ለምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የሚለዩና በምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ በሁሉም ወረዳዎች በአጀንዳ ልየታ የሚሳተፉ ተወካዮች መምረጣቸውን የጠቀሱት ኃላፊው መዲናዋን ጨምሮ የተሳታፊዎች ልየታ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች ለምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ለመለየት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ 700 ወረዳዎች ላይ የተሳታፊዎች ልየታ እየተከናወነ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ 327 ወረዳዎች የአጀንዳ ሀሳብ የሚሰጡ ተወካዮችን መመርጣቸውን ጠቁመዋል።

በአማራ እና በትግራይ ክልል ተሳታፊዎችን ለመለየት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ያነሱት አቶ ጥበቡ የተሳታፊዎች ልየታ ባልተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች በቀጣዮቹ ሳምንታት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል ፡፡