በአተገባበሩ ላይ ተቃውሞ ይቀርብበት የነበረውን የሚዲያ አዋጅ ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተቃውሞ ቀረበ፡፡

ረቂቅ አዋጁን በመቃወም 14 የጋዜጠኝነት ሙያ ማህበራት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡

እታገኘሁ መኮነን

ከሁለት ሳምንት በፊት ጥቅምት 19ቀን2017 ዓ.ም የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6ኛው ዙር 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ባካሄደው 2ኛ መደበኛ ስብሰባ፣የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013ን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ የሚታወቅ ነው፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ 14  የጋዜጠኝነት የሙያ ማህበራት እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቾች የአዋጁ ማሻሻያ አስፈላጊነት ላይ ገለልተኛ ጥናት ባልተደረገበት፣ በቂ የባለድርሻ አካላት ውይይትም ባልተካሔደበት ሁኔታ ረቂቁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ መቅረቡ፣ እንዲሁም በአዋጁ ከለላ ተሰጥቷቸው የነበሩ የቁጥጥርና ሚዛን መጠበቂያዎች በረቂቅ አዋጁ ሊሻሩ የሚችሉ መሆናቸው በእጅጉ አሳስቦናል በሚል የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡

ማህበራቱ በመግለጫቸው በአስፈፃሚው አካል ተረቅቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ የቀረበው ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ በሥራ ላይ የሚገኘውን የመገናኛ ብዙኃን ሕግ በርካታ አንቀፆች ይዘትና መንፈስ የሚቀይር ነው ብለዋል፡፡ ረቂቅ ማሻሻያው የአካሄድና የይዘት ግድፈቶች በስፋት የሚስተዋሉበት ሲሆን፣  በረቂቁ ማሻሻያ ላይ ምንም ዓይነት የሕዝብ ውይይቶች ባለመከናወናቸው የሲቪል ማኅበረሰቡን፣ የሚዲያ ሙያተኞችን እንዲሁም የሌሎች መብቶች ተሟጋቾችንና የማኅበረሰብ ድምፆች እንዳይሰሙ አድርጓል ሲሉም ቅሬታቸውን አንፀባርቀዋል። ማሻሻያውን ለማዘጋጀት የተሔደበት መንገድ ግልጽነትና አሳታፊነት የጎደለው ነው ያሉት ማህበራቱ የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት በገለልተኛ አካል በተሠራ ጥናት ስለመለየቱ የቀረበ ማስረጃም አለመኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል የረቂቅ አዋጁ የተለያዩ አንቀፆች  በሥራ ላይ የሚገኘው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጥበቃ የሚሰጣችውን ነጻነቶች የሚገድብና የሚዲያ ተቆጣጣሪውን አካል በአስፈፃሚው አካል ተፅዕኖ ውስጥ ይከተዋል የሚል ስጋት እንዳላቸውም አንስተዋል። የነባሩን አዋጅ አንቀጽ 8 (2) ዋና ዳይሬክተሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለሚሾምበት የሚደነግገው ክፍል፤ አንቀጽ 9 (1 እና 2) የቦርዱ አባላት እጩዎች የሚመለመሉበትና የሚፀድቁበት ሒደት ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበት የሚደነግገው ከፍል፤  አንቀጽ 11 (6) የቦርዱ አባላት ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ወይም ተቀጣሪነት የሚከለከሉበትን ሁኔታ የሚደነግገው ክፍል  መሰረዝ ዋና ዋና የይዘት ለውጦች መሆናቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡ በአዲሱ ማሻሻያ  የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሹመት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሰጠቱ፤ እንዲሁም በነባሩ አዋጅ ለቦርዱ ተሰጥተው የነበሩት የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት የመሳሰሉት ኃላፊነቶች አሁን ለባለሥልጣኑ መሰጠታቸው ሥልጣንን ጠቅልሎ ለአንድ አካል ከመስጠትና በሒደትም ላልተገባ ተፅዕኖ በር ከመክፈቱ በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሱት የማሻሻያው አንቀፆች በአንድነት ሲነበቡ የነባሩን አዋጅ አንቀጽ 7 (የባለሥልጣኑን ገለልተኝነትና ነፃነት) ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ረቂቅ አዋጅ ያደርገዋልብለዋ ማህበራቱ በመግለጫቸው።   

ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚቀርብበት ወቅት ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምክር ቤት አባላት ጭምር ተቃውሞ ገጥሞት የነበረ ቢሆንም በቂ የባለድርሻ አካላት ውይይት ሳይደረግበት ወደቋሚ ኮሚቴ መመራቱ በጉዳዩ ላይ የሕዝብን ድምፅ በተገቢ ሁኔታ ላለማካተቱ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል ያሉት የጋዜጠኝነት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማህበራት እኛ እንደ ህዝብ ድምጽነታችን ከረቂቅ አዋጁ ማሻሻያ ሒደት ጋር በተያያዘ በርካታ ጉዳዮች ያሳስቡናል፤ አስችኳይ መፍትሔም ሊፈለግላቸው እንደሚገባ በአጽንኦት ለማስገንዘብ እንወዳለን ብለዋል። ማህበራቱ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ በጥናት የተደገፈ ማስረጃ እንዲቀርብ እና በባለድርሻ ወገኖች ሰፊ ውይይትና  መግባባት እንዲደረስበት፣ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በምክር ቤቱ ከመፅደቁ በፊት ትርጉም ያለውና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት እንዲከናወን፣ የውይይቶቹ ግብዓቶች በአግባቡ ተካትትው ረቂቁ እንዲዳብር፣ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ መንፈስ ዴሞክራሲን ከማስፈንና የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነትን ከማረጋገጥ አንፃር የነበረውን አስቻይ የሕግ ማዕቀፍ የሚንድና ወደኋላ  የሚጎትት እንዳይሆን በአጽንኦት እንጠይቃለን ብለዋል።

 በኢትዮጵያ በ2010 ከተካሄደው የፖለቲካ ለውጥ ጋር ተያይዞ ከተደረጉት የህግ ማሻሻያዎች አንዱ    የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ነበር። የዚህ አዋጅ መጽደቅ በአገራችን ነጻና ገለልተኛ የሚዲያ ምኅዳር ለመገንባት ከፍተኛ ተስፋን አሳድሮ ነበር። ሆኖም የአዋጁ አተገባበር ላይ በርካታ ቅሬታዎች ሲነሱ ነበር ፡፡ በተለይም በአዋጁ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲ አባል እና የመንግስት ሹመት ላይ ያለ ግለሰብ የቦርድ አባል መሆን እንደማይችል የተጠቀሰው አንቀጽ ተሽሮ የቦርድ አባላት ሆነው ከተሾሙት ዘጠኝ አባላት መካከል አራቱ የፖለቲካ  ፓርቲ አባልና እና የምክር ቤት ተመራጭ ነበሩ፡፡በጊዜው ይህ ሹመት በፓርላማ ሲጸድቅ ሹመቱ “የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን የጣሰ ነው” የሚል ትችት ቀርቦበት ነበር፡፡ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበርን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማህበራት ሹመቱን በመቃወም መግለጫዎችን አውጥተው ነበር፡፡

ምንም እንኳ አዋጁ እንዲህ አይነት የአተገባበር ችግር ቢኖርበትም የአዋጁ ይዘት ከዓለም ዐቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ጋር የተጣጣመ እና ለፕሬስ ነጻነትና የተሻለ የሚዲያ ሥራ ለመስራት መሠረት መሆን ይችል ነበር፡፡

ሆኖም ይህንን አዋጅ ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በአዋጁ የሰፈሩ እና የሚዲያ ምህዳሩን የሚያሰፉ አንቀጾችን የሚሽር በመሆኑ ቀድሞም በችግር ውስጥ ለሚዳክረው የኢትዮጵያ ሚዲያ ሌላ ተጨማሪ እንቅፋት ይሆናል የሚል ግምት ተሰጥቶታል፡፡

መግለጫውን በትብብር ካወጡት ማህበራት መሃከል የህግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (LHR) ፣የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር (EMMPA)፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር (EMWA)፣የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)  ይገኙበታል፡፡