“የሚዲያ አዋጅ ማሻሻያ ” ወደፊት ወይስ ወደኋላ ?

እታገኘሁ መኮነን

የ2010ሩ ለውጥ እና የሚዲያው መነቃቃት

2010 ዓ.ም  ፤የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የሃገር ግንባታ ሂደት ላይ ከታዩት ለውጦች  መሃል አንዱ ለሚዲያው አንጻራዊ የሚባል ነጻ የመጫወቻ ሜዳ መፍቀድ ነበር ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም  2013 ላይ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ፀደቀ ፤የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013፡፡ ይሄ አዋጅ ከዛ ቀደም ብሎ ለ10 ዓመታት ያህል የሰራበትን የጋዜጠኝነት ሙያ በአፈና፣ በነጻነት ሃሳብን እና እውነትን መዘገብን በመነፈግ፣ በጫና እና ባለመመቸት ምክንያት ጥሎ ለመውጣት ለተገደደው ጋዜጠኛ ካህሳይ ብሩ እና የሙያ አጋሮቹ እንዲሁም ለመላው የሚዲያ ማህበረሰብ ፤ከዚያም ከፍ ሲል ደግሞ ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ ለሚያምኑ ለዚህም ለሚተጉ የሰብዓዊ መብት ዘቦች ሁሉ አስደሳች ዜና ነበር፡፡

ካህሳይ ከ2000ዓም-2009ዓ.ም ድረስ በድምፀ ወያኔ የሬድዮ ጣቢያ ከሪፖርተርነት እስከ ሥራ አስኪያጅነት ባሉ የስራ ድርሻዎች ውስጥ የሰራ ጋዜጠኛ ነው፡፡ሆኖም በስራ ላይ በነበረባቸው ዓመታት ሁሉ ሙያውን የሙያው ስነምግባር በሚያዘው መንገድ እንዳይከውን  ብዙ እንቅፋቶች ይገጥሙት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ሚዲያው የገዚዎች የፖለቲካ ገበጣ መጫወቻ ሜዳ ሁኖ ከላይ በሚወርድ ትዕዛዝ ብቻ የሚዘወር ሲሆንበት፤ ጫናው ሲበረታ 2009 ላይ በሚወደው ሙያው ተስፋ ቆርጦ ጋዜጠኝነትን ተሰናበተ፡፡ ወደ አክሱም ዩንቨርስቲም አምርቶ ጋዜጠኝነት ማስተማር ጀመረ፡፡ “ቢያንስ የሚዲያን ሚና እና ህግ የሚያውቁ፤ ለሙያቸው የሚታገሉ ተማሪዎችን ማብቃት አለብኝ ” ብዬ ነው ለማስተማር የወሰንኩት ይላል ካህሳይ የዛን ጊዜ ውሳኔውን ሲያስታውስ፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ግን 2010ዓ.ም የመንግስት “ስርዓተ ለውጥ” መጣ ፡፡ እሱን ተከትሎም የመገናኛ ብዙኃኑ አዋጁ ፀደቀ፡፡ በወቅቱ ሪፎርም ይደረግባቸዋል ከተባሉት ተቋማት አንዱ ሚዲያ ነበር ፡፡ የክልሉ ባለስልጣናትም የትግራይ ቲቪ ሥራ አስኪያጆችም “አሁን ሚዲያውን በነጻነት እንዲሰራ የምናደርግበት ፣ ሚዲያው የህዝብ ድምጽ የሚሆንበት ሙያዊ ነጻነት የሚከበርበት ጊዜ ነውና ሚዲያውን ተቀላቀል ”አሉት፡፡ ካህሳይ  በአዋጁ ላይ ትልቅ ተስፋ ጥሎ ነበርና የማስተማር ስራውን ትቶ ወደ ጋዜጠኝነት ተመለሰ፡፡በትግራይ ቲቪ ውስጥም የይዘት እና የዜና ክፍል ሃላፊ ሁኖ መስራት ጀመረ፡፡

ካህሳይ አዋጁ የጸደቀበትን እና ሥራ የጀመረበትን የመጀመሪያ ወራቶች ሲያስታውስ “እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት የተጋንበት የተገበርንበትም ጊዜ ነበር” ይላል፡፡ “ከዚህ ቀደም የክልሉ ገዢ ፓርቲ ብቻውን ይጠቀምበት የነበረውን የቴሌቭዥን ጣብያ ለሌሎች ወገኖች ጭምር ክፍት አድርገን እውነተኛ የህዝብ ድምጽ ሁነን መስራት ጀምረን ነበር ” ይላል ካህሳይ፡፡ “ይሄንን ነፃነት ደግሞ ያገኘነው አዋጁ በሰጠን መብት ነበር ”ይላል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር  ስራ አስፈጻሚ እና የሕግ ክፍል ሃላፊ ጋዜጠኛ ዳዊት ታደሰ በበኩሉ ከጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት በፊት በነበሩት ሦስት አስርታት በስልጣን ላይ የቆየው አፋኝ ስርዓት የነጻ ፕሬሱን ሥራ አታካች አድርጎት ነበር በማለት  የ2013ቱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ለብዙዎች ተስፋ ስለመስጠቱ አያጠያይቅም ይላል ፡፡ “ሚዲያው ቀን ወጣለት ያለው በርካታ ነው፡፡ እኔም በአዋጁ ተስፋ ከጣሉት መሃል ነበርኩ ”ይላል ዳዊት፡፡

ከተወሰኑ ወራት በኋላ ግን ሁኔታዎች የቀድሞ መልካቸውን መያዝ መጀመራቸውን የሚያስታውሰው ካህሳይ ሲውል ሲያድር አንሰራርቶ የነበረው የነጻ ሚዲያ መንፈስ በገዢዎች የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት መልሶ ወደነበረበት ማነቆ ቢገባም የአዋጁ መጽደቅ ግን ቢያንስ ሚዲያው የህግ ከለላ እንዳለው እንዲሰማን አድርጓናል ይላል፡፡ከካህሳይ ሃሳብ ጋር የሚስማማው ዳዊትም  ከጠ/ሚንስትር ዐቢይ የመጀመሪያው የስልጣን ዓመት በኋላ ያለው ጊዜ ለሚዲያውም ሆነ ለጋዜጠኞች ፈተና የበዛበት ነው በማለት አዋጁ መኖሩ ግን ቢያንስ የህግ ከለላ አግኝተናል ብለን እንድናስብ አድርጎናል ይላል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 የሚዲያ ነጻነትን በህግ ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ነው፡፡ በአዋጁ የመርቀቅ እና መጽደቅ ሂደት ላይ ተሳታፊ የነበሩት የህግ ባለሙያው አቶ ቁምላቸው በወቅቱ ይህንን አዋጅ የማርቀቅ ሂደቱ በጣም አሳታፊ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በፍትህ ሚ/ሚኒስትር ስር የተቋቋመ ነጻ የህግ ባለሙያዎች ያሉበት የህግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ተቋቁሞ የህግ ባለሙያዎች፣ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነት መምህራን፣ የሚዲያ  ባለሙያዎች ወዘተ ተካተውበት እንደተዘጋጀም ይናገራሉ፡፡ አዋጁ ከረቀቀ በኋላም በአለም አቀፍ ደረጃ የሚዲያ በተለይም የብሮድካስት ህግን ጠንቅቀው የሚያውቁ የህግ ባለሙያዎች እንዳዩት እና ዓለም አቀፍ የሚዲያ ህግ ደረጃን የሚያሟላ መሆኑም መረጋገጡንም በማስታወስ ተራማጅ አዋጅ ነበር ይላሉ፡፡

አዋጁ ከጸደቀ በኃላ ግን  አተገባበሩ ላይ በርካታ ቅሬታዎች ሲነሱ ነበር ፡፡ በተለይም በአዋጁ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲ አባል እና የመንግስት ሹመት ላይ ያለ ግለሰብ የቦርድ አባል መሆን እንደማይችል የተጠቀሰው አንቀጽ ተሽሮ የቦርድ አባላት ሆነው ከተሾሙት ዘጠኝ አባላት መካከል አራቱ የፖለቲካ  ፓርቲ አባልና እና የምክር ቤት ተመራጭ መሆናቸው ተቃውሞ አስነስቶ ነበር፡፡በጊዜው ይህ ሹመት በፓርላማ ሲጸድቅ ሹመቱ “የመገናኛ ብዙኃን አዋጁን የጣሰ ነው” የሚል ትችት ቀርቦበት ነበር፡፡ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበርን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማህበራት ሹመቱን በመቃወም መግለጫዎችን አውጥተው ነበር፡፡

በሂደትም በአዋጁ አንቀጽ 86/1 ላይ እንደሰፈረው በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የወንጀል  ድርጊት በመፈፀም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ያለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ወደፍርድ ቤት መቅረብ ቢኖርበትም  ላለፉት 4 ዓመታት ከ200 በላይ ጋዜጠኞች በሚዲያ ላይ በሰሩት ስራ በወንጀል ተጠርጥረው ወህኒ ወርደዋል፡፡ አሁን ድረስ  ለዓመታት በማረሚያ ቤት ታስረው ውሳኔ ሳያገኙ ፍርድ ቤት የሚመላለሱ ጋዜጠኞች አሉ፡፡ africanarguments በ2024 ባወጣው አንድ ዘገባ ላይ ከ 2019  እስከ ሰኔ 2024 ድረስ ብቻ በኢትዮጵያ  200 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል ይላል ፡፡ ከእስር በተጨማሪ በማን እና እንዴት እንደታገቱ ሳይታወቅ ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከስራ ቦታቸው እና ከመንገድ ላይ ተጠልፈው ተወስደው ለቀናት እና ለወራት ተሰውረው የተለቀቁ ጋዜጠኞችም ነበሩ፡፡ሁለት ጋዜጠኞች ደግሞ ተገድለዋል፡፡ ከ30 በላይ ጋዜጠኞች በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት ሃገርጥለው ለመሰደድም ተገደዋል፡፡ ይህም የአዋጁን ተፈፃሚነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተዋል፡፡

አዋጁ አተገባበሩ ላይ ባጋጠሙት ችግሮች ምክንያት  በተለይ የሚዲያ ማህበረሰቡን መብት በተገቢው መንገድ ማስከበር ባይችልም ችግሮች ሲፈጠሩ ከህግ አግባብ ውጭ መሆናቸውን በማስረጃ በማሳየት ለመሞገት እና የሚዲያውን ነጻነት ከማስከበር አንጻር የማይናቅ ሚና ያለው ዲሞክራሲያዊ አዋጅ ነበር ይላሉ አቶ ቁምላቸው፡፡

የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ማሻሻያ

አዋጁ ከጸደቀ ከአራት ኣመት በኋላ ጥቅምት 19 /2017 ዓም  የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የዚህን አዋጅ ማሻሻያ ይዞ ቀረበ፡፡ በወቅቱ አዋጁን ለምን ማሻሻል እንዳስፈለገ የተገለጸ ነገር አልነበረም፡፡

ዳዊት ታደሰ“ በቅድሚያ ማሻሻያው በዚህ ፍጥነት ለምን እንዳስፈለገ አልገባኝም፡፡ አዲሱ ከጸደቀ ገና ሶስት ዓመቱ ነው፡፡ አንድ አዋጅ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሲሻሻል አላየሁም፡፡ ሌላው፣ የ2013ቱ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት እንደነበረው የሚመለከታቸው ግለሰቦችና ተቋማት ተሳትፎን አለማየቴ ነው፡፡ ያኛው ላይ የጋዜጠኞች ማህበራት፣ የህግ ባለሙያዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎችም የነበራቸው አስተዋጽኦ ልዩ ነበረ፡፡ አሁን ግን ማሻሻያው ወደፓርላማ እስኪመራ ድረስ አልሰማንም ”ይላል፡፡  ከዳዊት ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ያጋራችን የኢትዮጵያ ሴት የመገና ኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር የቦርድ አባል የሆነችው ጋዜጠኛ መልካምሰው ሰለሞን ዲሞክራሲያዊና ሚዲያውን ጠባቂ የነበረን ህግ በዚህ ፍጥነት “ማሻሻል ”በሚል ምክንያት መቀየር ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም ትላለች፡፡

ይህንን  ተከትሎ 14 የሚሆኑ የጋዜጠኝነት ሙያ ማህበራት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የአዋጁን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በመቃወም በጋራ መግለጫ ማውጣታቸውም ይታወሳል፡፡

ከተቃውሞ መግለጫው በኃላ የሚመለከታቸውን አካላት ለማወያየት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ  ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተካፈሉት አቶ ቁምላቸው በውይይት መድረኩ ላይ  የማሻሻያው ክፍተቶች እና ችግሮች ቢነሱም የተሰጠው ምላሽ ግን አጥጋቢ እና አሳማኝ አልነበረም ይላሉ፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበረችው መልካምሰው በዕለቱ በተለይ የቦርድ አባላትን አመራረጥ በተመለከተ ከፍተኛ ተቃውሞ ከተሳታፊዎች መነሳቱን ታስታውሳለች ፡፡የቦርዱን ስልጣን ጠቅልሎ ለአንድ አካል መስጠትስ ተገቢ ነው ወይ? የሚል ጥያቄም መቅረቡን እንዲሁ፡፡ ቀደም  ሲል የቦርዱ ስልጣን የነበረው የመገናኛ ብዙኃንን ፈቃድ የመሰረዝ እና ያለማደስ መብት ለባለስልጣኑ መሰጠቱ አግባብነት  የሌለው እና ተጠያቂነትን የሚያጠፋ አሰራር ነው የሚል ጥያቄ ስናነሳ  “ቦርዱ ለረዥም ጊዜ ቶሎ ቶሎ ለመሰብሰብ እና ችግሮችን ለመፍታት የማይችል በመሆኑ ይህንን ለማስቀረት ሲባል ማሻሻያው አስፈልጓል” የሚል ምላሽ ተሰጠን የምትለው መልካምሰው የቦርዱ አባላት ይህንን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ካልነበረ አባላቱን እንጂ ህጉን መቀየር ለምን አስፈለገ ትላለች ፡፡

ለመሆኑ የሚሻሻሉ የተባሉት የአዋጁ ዋና ዋና ክፍሎች የትኞቹ ናቸው ?

የነባሩ አዋጅ አንቀጽ 8 (2) ዋና ዳይሬክተሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለሚሾምበት የሚደነግገው ክፍል፤ አንቀጽ 9 (1 እና 2) የቦርዱ አባላት እጩዎች የሚመለመሉበትና የሚፀድቁበት ሒደት ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበት የሚደነግገው ከፍል፤  አንቀጽ 11 (6) የቦርዱ አባላት ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ወይም ተቀጣሪነት የሚከለከሉበትን ሁኔታ የሚደነግገው ክፍል  መሰረዝ ዋና ዋና የይዘት ለውጦች መሆናቸውን በምሳሌነት የሚያነሱት የህግ ባለሙያው አቶ ቁምላቸው በአዲሱ ማሻሻያ  የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሹመት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሰጠቱ፤ እንዲሁም በነባሩ አዋጅ ለቦርዱ ተሰጥተው የነበሩት የፈቃድ ወይም የምዝገባ ምስክር ወረቀት አለማደስ፣ ማገድ፣ መሰረዝ፣ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት የመሳሰሉት ኃላፊነቶች አሁን ለባለሥልጣኑ መሰጠታቸው ሥልጣንን ጠቅልሎ ለአንድ አካል ከመስጠትና በሒደትም ላልተገባ ተፅዕኖ በር ከመክፈቱ በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሱት የማሻሻያው አንቀፆች በአንድነት ሲነበቡ የነባሩን አዋጅ አንቀጽ 7 (የባለሥልጣኑን ገለልተኝነትና ነፃነት) ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ረቂቅ አዋጅ ያደርገዋል ይላሉ  ፡፡

አሁን በተግባር ላይ ባለው አዋጅ መሰረት ከዘጠኙ የቦርድ አባላት ሁለቱ ከሲቪክ ማህበራት፣ ሁለቱ ቀጥታ ከመገናኛ ብዙኃን ፣ሁለቱ ለመገናኛ ብዙኃን ቅርበት ካላቸው አካላት የሚወከሉ ነበሩ፡፡ አሁን በማሻሻያው መሰረት የቦርድ አባላት የሚመለመሉበትን መስፈር የያዘው አንቀጽ 11(6) እንዲሰረዛ ተደርጓል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ያለገደብ እንደሳተፉ ዕድል ተሰጣቸው ማለት የገዢው ፓርቲ አባላት ሚዲያ ላይ የፈለጉትን ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ዕድል መስጠት  ነው የሚሉት ባለሙያው የመገናኛ ብዙኃን ውክልና ቀሪ ተደረገ ማለት ደግሞ ፕረሱን ለጥቃት የሚያጋልጥ ተቃራኒ ውጤትን ይዞ እንደሚመጣ አልጠራጠርም ይላሉ፡፡

ይሄንን አዋጅ ስናዘጋጅ ፈቃድ ያለማደስን እና የመሰረዝን ስልጣን ለቦርዱ አድርገንበት የነበረው ዋነኛ ምክንያት የመገናኛ ብዙኃን የፈቃድ ጉዳይ መሰረታዊ የሆነውን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ህገ መንግስታዊ መብት የሚመለከት በመሆኑ ይሄንን በሚመለከት ማንኛውም አይነት ርምጃ ሊወሰድ የሚገባው በገለልተኛ አካል ነው በማለት ነበር የሚሉት አቶ ቁምላቸው አሁን ይሄ ስልጣን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሆነ ስልጣኑ ገለልተኛ ባልሆነ አካል እጅ ስር ወደቀቀ ማለት ነው በማለት ያብራራሉ፡፡

ሌላው በማሻሻያው ላይ የተካተተው አወዛጋቢ አንቀጽ የቀጥታ ስርጭት ላይ ለሚፈጠር ማንኛውም ስህተት ጋዜጠኛው እና  ሚዲያው ተጠያቂ የሚሆንበት ክፍል ነው፡፡ በማሻሻያው ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው በቀጥታ ስርጭት ወቅት ለሚፈጠር ማንኛውም የህግ ጥሰት ጋዜጠኛው እና ሚዲያው በህግ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ጋዜጠኛ በአንድ ጉዳይ ላይ በቀጥታ ስርጭት ወቅት የሚያናግረውን ወይም የሚያቀርበውን እንግዳ ንግግር አስቀድሞ እንዴት ማወቅ እና መቆጣጠር ይችላል የምትለው “ሌላ ሰው በተናገረው ስህተት ጋዜጠኛውን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ያልሆነ አሰራር ነው” ትላለች፡፡መልካም ሰው “ተጠያቂነትን በመሸሽ ጋዜጠኛው የሰዎችን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን እንዲገድብ ይገደዳል ይሄ ደግሞ ከጋዜጠኛ የሚጠበቅ አይደለም” የምትለው ጋዜጠኛ መልካም ሰው
ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኛው ተጠያቂ ላለመሆን  ሃሳብ የሚሰጠውን ሰው አየር ላይ የሚያርም ወይም የተናገረው ነገር ልክ አለመሆኑን በመጥቀስ የሚያስተባብል ከሆነ ከጋዜጠኝነት መርህ በተቃራኒ  የራሱን አስተሳሰብ ሊያንጸባርቅ እንዲሁም የአድማጭ ተመልካቾቹን መረጃ የማግኘት መብትም ሊገድብ  ነው በማለት ማሻሻየው አግባብ እንዳልሆነ ታስረዳለች፡፡ ከዚህ ይልቅ  ምህዳሩን በማስፋት ሃሳቦች ቢንሸራሸሩ ፤በአንድ ቀጥታ ስርጭት ወቅት አንድ ሃሳብ ያንጸባረቀ እንግዳ ቢቀርብ በቀጣይ ሌላኛውን ጎን የሚያሳይ እንግዳ በማቅረብ ሚዛናዊ መረጃን ማድረስ እንጂ ሃሳብን መገደብ ልክ አይደለም ትላለች፡፡ ማህበረሰቡም የተለያዩ አስተሳሰቦችን የማድመጥ ዕድል ሊነፈግ አይገባም የምትለው መልካም ሚዲያ ሃሳብ የማንሸራሸሪያ መድረክ በመሆኑ ሳይሸማቀቅ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እና መረጃን እና እውነትን የመዘገብ ስራውንእንዲሰራ ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርለት ይገባል ትላለች፡፡

ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መሰረታዊ ህገመንግስታዊ መብት ስለሆነ እና ለዲሞክራያዊ ስርዓት መሰረት ስለሆነ በገለልተኛ አካል መጠበቅ አለበት የሚሉት አቶ ቁምላቸው የሚዲያ ጉዳይ የጋዜጠኝነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህዝብ መረጃን የማግኘት መብት ጭምር በመሆኑ ሚዲያ ለሌሎች መብቶች ቁልፍ መሳሪያ ነው ይላሉ፤ስለሆነም ዲሞከራሲያዊ ስርዓትን እገነባለሁ የሚል መንግስት የሚዲያን መብት ማክበር እንዳለበት በማስረዳት ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተፈረመው የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 19 ላይም ሆነ በሃገሪቱ ህገመንግስት ላይ በግልጽ የሰፈረ በመሆኑ ይህንን መብት ለመገደብ የሚወጡ ህጎች የዲሞክራሲ እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ  መብትን የሚጻረሩ ህጎች ተደርገው ይወሰዳሉ ይላሉ፡፡እናም ይህንን ማሻሻያ መቀበል ሚዲያውን መሉ በሙሉ ማፈን ማለት ነው ይላሉ  አቶ ቁምላቸው፡፡

ዳዊት በበኩሉ ይህ ማሻሻያ ከጸደቀ በግሌ በኢትዮጵያ ፕሬስ ላይ የነበረኝ ጭላንጭል ተስፋ እንደጨለመ እቆጥረዋለሁ ይላል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን እና ይተገበራል የተባለውን ሪፎርም ተስፋ አድርጎ  ወደ ጋዜጠኝነት የተመለሰው ካህሳይም  በክልሉ በነበረው ያላባራ የፖለቲካ ሽኩቻ ከስራ ከመፈናቀል እስከ ተደጋጋሚ እስር  አስተናግዶ በመጨረሻ ስራውንም የሶስተኛ ድግሪ ትምህርቱንም ትቶ  ወደ አዲስ አበባ መጥቷል፡፡ ዛሬ ካህሳይ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለለትን የጋዜጠኝነት ስራ ለመስራት ዕድል ተነፍጎት ራይድ እየሰራ ራሱን እና ቤተሰቡን ያስተዳድራል፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያ ረዥም ዓመት እንደቆየ እና ለሙያው መስዋዕትነት እንደደከፈለ አንድ ሰው ይህ አዋጅ ማሻሻያ በሚል ሰበብ ከተሻረ እኔም በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ የነበረኝ ተስፋ ጨርሶ ይሟጠጣል ይላል፡፡

የአዋጁን ማሻሻያ በመቃወም መግለጫ ካወጡት ተቋማት መሃል የተወሰኑትን መንግስት ከቀናት በኋላ ማገዱ ደግሞ መንግስት በማሻሻያው ላይ ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ ምልክት ሁኗል፡፡