እታገኘሁ መኮነን

አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች መፈናቀሎች እና እገታዎች በሚስተዋሉበት ትግራይ ክልል ደግሞ ሙሉ በሙሉ ራሱን ባገለለበት ፤ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከዘገባ በታገዱበት ወቅት የተካሄደው የ2018ቱ ሃገራዊ ምርጫ ፤ ከአፍሪካ እና ከሃገር ውስጥ ታዛቢዎች ሙገሳን ከአንዳንድ የውጭ ታዛቢዎች እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ወቀሳን አስተናግዶ አልፏል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት ምርጫውን እንዳይዘግቡ ለታገዱ የውጭ ሚዲያዎች ፈቃድ እንዲሰጥ አስቀድሞ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም፡፡
በታዛቢነት እንዲገኙ የተፈቀደላቸው የአፍሪካ ህብረት ታዛቢዎች እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምርጫው አለም አቀፍ መርሆዎችን ባከበረ መልኩ የተከናወነ ነው ሲሉ ምስክርነት ችረዋል፡፡አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልልሎች ውስጥ በመንግስት ቢሮ የሚሰሩ ሰራተኞች በተደጋጋሚ ጫና ምክንያት ካርድ አውጥተው ለመምረጥ እንደተገደዱ እንዲሁም በተለያዩ ማዕቀፎች ውስጥ ያሉ ዜጎችም ከገዚው ፓርቲ ብልጽግና ስራ አስፈጻሚዎች ካርድ እንደዲያወጡ ቤት ለቤት ጭምር በተደረገ አሰሳ ጫና እና የስነልቦና ተጽዕኖ እንዳደረባቸውም ሲነገሩ ተደምጧል፡፡ ይህ ሲደማመር የምርጫውን ቅቡልነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ከቶታል፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ኦሮሚያ ክልል ባለው የፀጥታ ሁኔታ እና ጠባብ የፖለቲካ ምኅዳር ለምርጫ የሚጋብዝ ስላልሆነ በአዲስ አበባ ብቻ ለመወዳደር እንደተገደደ ተናግሯል፡፡
የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከቢቢሲ አማረኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ምርጫው “በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዝቅተኛ ፉክክር የሚካሄድበት” እንደሆነ በመግለጽ “የምንሳተፈው ሕጉ በተከታታይ በምርጫ አለመሳተፍን ስለማይፈቅድ ከፓርቲነት እንዳንሰረዝ ነው ብለዋል፡፡
የሮይተርስ የዜና ወኪል ሦስት ጋዜጠኞች ፈቃድ መሰረዙን ተከትሎ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ “በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እና ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን ላይ አፋኝ የሆነ የቁጥጥር እርምጃ መተግበሩ አሳሳቢ አካሄድ ነው” ማለቱም ይታወሳል።
በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ከሚፈጠሩ ግጭቶች በተጨማሪ ነዋሪዎች እና መንገደኞች በታጣቂዎች መታገታቸው እና መገደላቸውም በተለያየ ወቅት ሲዘገብ ቆይቷል።
በአማራ ክልል በፋኖ ኃይሎች እና በመንግሥት መካከል በቀጠለው ግጭትም በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በግጭቶች የተነሳ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
በምርጫው ማግስት በአሪሲ ዞን አሰኮ ወረዳ በኦርዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ላይ የተፈጸመው ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ ደግሞ መንግስት ሰላም የማስከበር እና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ስራውን በአግባቡ እየሰራ እንዳልሆነ እና በሌሎች ስራዎች ላይ መጠመዱን የሚያሳይ ነው የሚሉ ቁጣዎችን ቀስቅሷል፡፡
