ምዕራብና የደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው ተተነበየ

ይህ ይፋ የተደረገው የኢትዮጲያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የወቅቱን ትንበያ ይፋ ለማድረግ ባዘጋጀው የባለድርሻ አካለት መድረክ ነው። በመድረኩም ያለፈውን የበጋ ወቅት ትንበያ የገመገመ ሲሆን በጋው በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደተስተዋለባቸውና ይህም ሁኔታ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ለሚገኙ አርሶ እና አርብቶ አደሮች ምቹ ሁኔታን የፈጠረ እንደነበረ ተገልጿል፡፡ በእለቱ የመጪው በልግ ትንበያ ይፋ የተደረገ ሲሆን በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍል መደበኛና ከመደበኛ በታች፤ የቦረናና ጉጂ ዞኖች፤ የሲዳማ፤ የማዕከላዊና የደቡብ ኢትዮጵያ መደበኛና ከመደበኛ በላይ፤ በሌላ በኩል የደቡብ ትግራይ፤ የምስራቅ አማራ፤ አፋር፤ መካከለኛው እና የምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚኖር ተጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩል የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው የተጠቆመ ሲሆን በተጨማሪም የምዕራብ አማራና የጥቂት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሰሜናዊ ክፍል አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ዝናብ እንደሚያገኙ በመድረኩ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከመደበኛው አንፃራዊ መጨመር እንደሚኖረው ገለፃ ተደርጓል፡፡

በመሆኑም ኢንስቲትዩቱ በየወቅቱ የሚሰጣቸውን የቅድመ ማስጠንቀቂያና የትንበያ መረጃዎችን ኅብረተሰቡ በሚገባ እንዲከታተልና ጥቅም ላይ እንዲያውል ተጠይቋል።