የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጥር 1 ቀን 2017 ባካሄደው ስብሰባ መንግሥት ከተመነው የመሸጫ ዋጋ በላይ ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እና እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር እንዲቀጡ የሚያደርግ አዋጅ አጽድቋል፡፡
በአዋጁ መሠረት ከመሸጫ ዋጋ በላይ በመሸጥ የሚፈጸም የመጀመሪያ ጥፋት ከሦስት መቶ ሃምሳ ሺህ እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር ያስቀጣል።ድርጊቱ በተደጋጋሚ ከተፈጸመ ከገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚኖር በአዋጁ ተደንግጓል።
ድርጊቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲፈጸም ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የሚያስቀጣ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ ከተፈጸመ ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት እስራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ ያስቀጣል።
የነዳጅ ምርቶችን “ሆን ብሎ” ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ለግብይት ማቅረብ ከአምስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እሥራት እና ከ350 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ አዋጁ ላይ ሰፍሯል።
ከዚህም በተጨማሪ በአዋጁ መሰረት የነዳጅ ውጤቶች ከተፈቀደለት የማጓጓዣ መስመር ውጪ ማጓጓዝ፣ ከተፈቀደለት ማራገፊያ ስፍራ ውጪ ማራገፍ ወይም ወደ ጎረቤት ሀገር በኮንትሮባንድ ማጓጓዝ፤ ከአምስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት እና ከ400 ሺህ እስከ 700 ሺህ ብር ያስቀጣል።እንዲሁም ከሚመለከተው አካል በጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኝ የነዳጅ ውጤቶችን የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች መሸጥ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ300 እስከ 500 ሺህ ብር ያስቀጣል፡፡የነዳጅ መቅጃ መሳሪያዎች የልኬት ሜትር ማስተካከያ ተደርጎበት በፕሎምፕ የታሰረውን መቁረጥ ወይም ልኬቱን ማዛባትም በተመሳሳይ ከ350 እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ አዋጁ ደንግጓል።
የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣንን ወይም የሚመለከተውን አካል የቁጥጥር ሂደት መቃወም እና ማሰናከል ደግሞ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ እስራት እና ከ200 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ያስቀጣል። በተጨማሪም “ማንኛውም የነዳጅ ውጤቶች አጓጓዥ ተሸከርካሪ ጂፒኤስ የመግጠም ግዴታ አለበት” የሚል አዲስ ድንጋጌ ተካትቶበታል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ይህ የአዋጁ የቅጣት ድንጋጌ “በሥራ ላይ ካለው የወንጀል ሕግ ጋር እንዴት ይታያል?” የሚል ጥያቄ አንሰተዋል።በነዳጅ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የመንግስት ባለስልጣናት እጅ አለበትም ተብሏል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ “ቅጣቶቹ በጣም የተጋነኑ ሁነው ነው ያየኋቸው” ሲሉ ተደምጠዋል። ዶ/ር ደሳለኝ አክለውም “አዋጁ ቅጣት ላይ ብቻ ያተኮረ፤ ቅጣትን ማዕከል ያደረገ ነው” ብለዋል።
ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ፤ “ቅጣቱ ከፍተኛ አይደለም” ብለዋል። “ነዳጁ ተሽጦ የሚገኘውን ትርፍ መጠን እና ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ስናይ እዚህ ላይ የተቀመጡት የገንዘብ ቅጣቶ ች በጣም ትንሽ ናቸው” ሲሉ መልሰዋል።
“የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ሥርዓት ለመደንገግ” የወጣው ይህ አዋጅ፤ በሁለት የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ እና በአንድ አባል ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
