የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ፀሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ያለ ስምምነት የተጠናቀቀውን የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የሰላም ድርድርን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ አውጥተዋል።
ዶ/ር ወርቅነህ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ውይይት እና ድርድር ያለውን ወሳኝ ሚና እንደሚገነዘቡ ገልጸዋል።
ኢጋድ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሰላም ውይይት ላይ በቅርበት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ በማንኛውም የድርድር ሂደት ውስጥ የማይቀር የፈተና ጊዜያት እንዳሉ እንደሚገነዘቡ መሰል የሽምግልና ሂደቶችን ልምድ በመንተራስ ገልጸዋል።
ዶ/ር ወርቅነህ ሁለቱም ተደራዳሪ ቡድኖች አለመግባባቶችን ለመፍታት ሰላማዊ ውይይት ማድረጋቸውን አመስግነው ለኢጋድ የቴክኒክ ቡድን እና ታዛቢዎች በተለይ ደግሞ የአሜሪካ እና የኖርዌይ ተወካዮች በውይይቱ ላይ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የውይይቱን ቦታ ላሰናዳው ለታንዛኒያ መንግስት ያላቸውን አድናቆትም ገልጸዋል።
ስራ አስፈፃሚው ሁሉም ወገኖች የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም በማስጠበቅ ለሰላሙ ሂደት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም፤ ቀሪ ችግሮችን ለመፍታት ሁለቱም ወገኖች ሌላ አዲስ ዙር ውይይት ይጀምራሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ኢጋድ በመንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል ያለው ችግር ተፈትቶ ሰላም እንዲሰፍን አሁንም እንደሚሰራ የገለፀ ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ሁኔታውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የማያቋርጥ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል።
ኢጋድ በታንዛኒያው ድርድር መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በምን በምን ጉዳዮች እንዳልተስማሙ እንዲሁም አሉ ያላቸውን ቀሪ ችግሮች በይፋ አላብራራም።
በኦሮሚያ ያለው ግጭት እልባት እንዲያገኝ የሰላም ድርድር በማማቻቸትና በመምራት ረገድ ኢጋድ ከፍተኛውን ድርሻ እንደተወጣ በስፋት ተዘግቧል።
