በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል በታንዛኒያዋ ዳሬሰላም ከተማ ለቀናት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያለውጤት መበተኑን መንግሥት አስታወቀ።
ይህንን ያሳወቁት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እና መንግሥትን ወክልው በድርድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ናቸው።
አምባሳደር ሬድዋን በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ላይ ማክሰኞ ኅዳር 11/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ ባሰራጩት መልዕክት እንዳሉት ሲካሄድ የሰነበተው ድርድር ካለስምምነት በመጠናቀቁ የኢትዮጵያ መንግሥት ማዘኑን አመልክተዋል።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በታንዛኒያ የመዝናኛ ደሴት ዛንዚባር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግሥት እና በአማጺው መካከል በተመሳሳይ ለቀናት የቆየ ድርድር ሲካሄድ ቆይቶ ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
ሁለተኛው ዙር ድርድር ሁለት ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ በታንዛኒያ ዋና ከተማዋ ዳሬሰላም ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፣ ከመጀመሪያው ዙር ድርድር በተለየ ሁኔታ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዦች እና የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎች የተሳተፉበት ነበር።
በተለይ ባለፈው ሳምንት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በድርድሩ ተሳታፊ መሆናቸው ከተሰማ በኋላ በበርካቶች ዘንድ ከስምምነት ሊደረስ ይችላል የሚል ተስፋ ተፈጥሮ ነበር።
አምባሳደር ሬድዋን እንዳሉት መንግሥት ጦርነት ቆሞ በዚህ ሳቢያ ሲደርስ የቆየው ጉዳት እና ውድመት እንዲቆም ካለፈው ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ጠቅሰው፣ በላላኛው ወገን ግትር ፍላጎት ከስምምነት ሳይደረስ መቅረቱን ገልጸዋል።
“ሌላኛው ወገን [የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት] ተጨባጭ ሁኔታን መሠረት ያላደረገ ፍላጎቶችን በማቅረቡ እና አደናቃፊ አካሄድን በመከተሉ ምክንያት” ንግግሩ ከስኬት ሳይደርስ ለመቋጨቱ ምክንያት እንደሆነ አምባሳደር ሬድዋን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሁለቱን ወገኖች ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ያደረጓቸው ጉዳዮች የትኞቹ እንደሆኑ ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።
አክለውም ከዚህ ቀደም እንዳካሄደው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥት የሠላም ስምምነቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እና ሕገ መንግሥትን ባከበረ ሁኔታ ከስምምነት እንዲደረስ ጽኑ ፍላጎትን ይዞ ከስምምነት ለመድረስ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የሚደረገው ድርድር ያለ ስምምነት መበተኑን ቢገልጽም ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከሁለት ዓመት በፊት በሽብርተኛ ቡድንነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈረጀ መሆኑ ይታወቃል።አማጺው ቡድን በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሲሆን፣ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።

በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች እየተባባሱ ይገኘሉ።በመጀመሪያው ዙር ንግግር ኬንያ እና ኖርዌይ የአሸማጋይነት ስፍራ የነበራቸው ሲሆን የአሜሪካ ዲፕሎማቶችም ድጋፍ እየሰጡ ኢጋድ የማሸማገሉን ሚና ሲጫወቱ እንደነበረ ተዘግቦ ነበር።
በፌደራሉ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሲካሄድ በነበረው የመጀመሪያው ንግግር ሁለቱን አካላት ካላስማሙ ጉዳዮች መካከል አንዱ የጋራ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ መሆኑን ተገልጾ ነበር።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስን እና ብልጽግናን ጨምሮ ሌሎች ፓለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ የጋራ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ጠይቆ ነበር።
ይሁን እንጂ መንግሥት ይህን ጥያቄ ውድቅ በማድረጉ የመጀመሪያው ዙር ንግግር ከቀናት ቆይታ በኋላ ያለ ስምምነት መበተኑ ይታወሳል።
