በደብረማርቆስ ከጸጥታ እክል ጋር በተያያዘ ወላድ እናቶች ለችግር ተዳርገዋል

ለአለም

በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች በማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሆነ ነዋሪዎች ለአዲስ ጊዜ ገለጹ።

ግጭቱ ተደጋግሞ እያጋጠመ ባለበት በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ  ከተማ ነዋሪ እንደሆኑ የሚናገሩት ወ/ሮ  ማዕረግ  ሞላ በሚኖሩበት አካባቢ በተከሰተው ጦርነት ይበልጥ ተጎጂ እየሆኑ ያሉት እናቶችና ህፃናት እንደሆኑ ተናግረዋል።

በደብረ ማርቆስ ዙሪያ ረቡዕ ገበያ ነዋሪ የሆኑት የጤና ባለሞያ አቶ አለምእሸት ስንሻው በበኩላቸው የመድሀኒት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እጥረት እየታየበት መሆኑን ገልፀው በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የጤና ጣቢያዎችን በቋሚነት ለመክፈት መቸገራቸውን ገልፀዋል።
በዚህም ሳቢያ እናቶች በቤታቸው ለመውለድ እንደተገደዱ የሚገልፁት የጤና ባለሞያው፤ በተለይ የደረሱ ሴቶች በእርግዝና ወራት ሊያገኙት የሚገባ የጤና ክትትል በበቂ ሁኔታ ባለመውሰዳቸው ከፍተኛ የጤና ችግር ላይ እንደወደቁ መስክረዋል።

ለወላድ እናቶችም ሆነ ለልጆቻቸው ጤና በቂ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚገልፁት በደብረማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል የጤና መኮንን አቶ አፈወርቅ ባለው፤ የተከሰተው ግጭት ግን ይሄንን ለማድረግ አስቻይ አለመሆኑን በማንሳት ብዙሀኑን እናት ቤት እንዲወልዱ ማስገደዱን ለአዲስ ጊዜ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ በዓመት 14 ሺህ የሚሆኑ እናቶች በወሊድ ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ እንዲሁም ከ87 ሺህ በላይ ጨቅላ ህፃናት በወሊድ ላይ በሚከሰት የጤና እክል ህይወታቸው እንደሚያልፍ የሚጠቁመውን የጤና ሚኒስቴር ጥናት ያስታወሱት አቶ አፈወርቅ በአማራ ክልል ያለው ግጭት በዚሁ ከቀጠለ ከላይ የተጠቀሰው ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ስጋት እንዳለቸው ለአዲስ ጊዜ ተናግረዋል።