በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ መንገደኞች ቤተሰቦች ቦይንግ በወንጀል እንዲከሰስ ጠየቁ

በኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን ከአምስት ዓመት በፊት ሕይወታቸውን ያጡ መንገደኞች ቤተሰቦች ለአደጋው መንስዔ የሆነው የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሠረት የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤትን ጠየቁ።

የመንገደኞቹ ቤተሰቦች በዋሽንግተን ከአሜሪካ የፍትህ ባለሥልጣናት ጋር ሚያዝያ 16/ 2016 ዓ.ም በተነጋገሩበት ወቅት የአሜሪካው ኩባንያ ቦይንግ ለፍርድ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

የተጎጂዎች ቤተሰቦች እና ተወካይ ጠበቆቻቸው ኩባንያው የሚያመርታቸውን አውሮፕላን ምርቶች ደኅንነት እና ጥራት ለማስጠበቅ ከሦስት ዓመት በፊት ከአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ጋር የገባውን የቁጥጥር መርሃ ግብር ስምምነት ጥሷል ብለዋል።

የ157 ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈው ከኢትዮጵያው አደጋ በተጨማሪ ለ189 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት በሆነው የኢንዶኔዥያ አየር መንገድ አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ቦይንግ በወንጀል እንዲጠየቅ ለፍትህ መሥሪያ ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸው ተገልጿል።

በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው አሰቃቂ በተባለው በቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን አደጋዎች የ346 ሰዎች ሕይወት አልፏል።

በሁለቱ አውሮፕላን አደጋዎች ሕይወታቸውን ያጡ ተሳፋሪዎች ቤተሰቦች በቅርቡ ንብረትነቱ የአሜሪካ አላስካ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን በበረራ ላይ ሳለ መስኮቱ መገንጠሉ ጋር ተያይዞ አሁንም የደኅንነት እና የጥራት ችግር እንዳለበት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት በአውሮፕላንን አምራቹ ላይ ካደረገው የረዥም ጊዜ ምርመራ በኋላ ቦይንግ ለ737 ማክስ አውሮፕላኑ ፍቃድ ለማግኘት ሲል ሆን ብሎ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ተቆጣጣሪዎችን እንዳሳሳተ ደርሸበታለሁ በሚል “አሜሪካን ለማጭበርበር በማሴር” በሚል ከሦስት ዓመት በፊት ክስ መስርቶበት ነበር።

ቦይንግ ቺካጎ በነበረው የፍርድ ሂደት በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ መንገደኞች ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ተስማምቶ በምላሹም የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ለአውሮፕላን አምራቹ ከ737 ማክስ ዲዛይን ጉድለት ጋር በተያያዘ በማጭበርበር ሴራ በወንጀል እንዳይከሰስ ከለላ ሰጥቶት ነበር።

የአውሮፕላን አምራቹ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድ እና ተጠያቂነቱን ተቀብሎ ለአሜሪካ መንግሥት፣ አደጋ ለደረሰባቸው አየር መንገዶች እና ለተጎጂዎች የሚሆን 2.5 ቢሊዮን ዶላር የቅጣት ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።

ቦይንግ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል ከአሜሪካ ዐቃቢያነ ሕጎች ጋር የደረሰው ስምምነት ኩባንያው በአደጋው ዙሪያ የሚካሄደው የወንጀል ምርመራ እንዲቀር የተስማማበት ነው።

በወቅቱም የፌደራል ዐቃቢያነ ሕጎች ቦይንግ ለመጪው ሦስት ዓመታት ያህል ለስምምነቱ ተገዢ ከሆነ የወንጀል ክሱን ለመተው ተስማምተው ነበር።

ነገር ግን የአላስካው አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ 9 በር ስምምነቱ ጊዜው ከማለፉ ከሁለት ቀናት በፊት ታኅሣሥ 26/ 2016 ዓ.ም. ተገንጥሎ በአየር ላይ መውደቁን ተከትሎ ሁኔታውን ቀይሮታል።

የፍትህ መሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣናት የአላስካውን ክስተት ቦይንግ ስምምነቱን ጥሶ ሊሆን ይችላል በሚል ሰፊ ምርመራ ለማድረግ እያጤኑት እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።

ከኦሬገን ግዛት ፖርትላንድ ከተማ ተነስቶ ወደ ካሊፎርኒያ ሲበር የነበረው አዲስ ሞዴል የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከተነሳ በኋላ የኋላ በሩ በበረራ ላይ እያለ ተገንጥሎ መውደቁን ተከትሎ በርካታ አየር መንገዶች አውሮፕላኑን እንዳይበር ማገዳቸው ይታወሳል።

ረቡዕ ለአምስት ሰዓታት ከቆየው ውይይት በኋላ የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ከዓመታት በፊት ከአውሮፕላን አምራቹ ጋር የተደረሰውን በወንጀል ያለመከሰስ ስምምነት አንስቶ ክሱን እንደገና ይጀምር ወይስ ያቋርጥ በሚለው ላይ ተጨማሪ መረጃ እንዳልተገኘ የተጎጂ ቤተሰቦችን የወከሉ ጠበቆች መናገራቸው ተዘግቧል።

የተጎጂ ቤተሰቦች ቦይንግ ታዛዥ ለመሆን የገባውን ስምምነት ጥሶ መሆኑን ለመከተታተል ነጻ ተቆጣጣሪ እንደሚያስፈልግ ይከራከራሉ።

ከሌሎች ኩባንያዎች በተለየ የፍትህ መሥሪያ ቤቱ ከቦይንግ ጋር ያደረገው ስምምነት እንዲህ ዓይነት መስፈርት አላስቀመጠም።

“የውጭ ተቆጣጣሪ ቢኖር የአላስካው ክስተት አይፈጠርም ነበር” ሲሉ በኢትዮጵያው አየር መንገድ አደጋ ልጃቸውን ያጡት ናዲያ ሚለሮን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ቦይንግ እንዲሁም የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ከተጎጂ ቤተሰቦች ጠበቆች ጋር በነበረ ውይይት፣ ቦይንግ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን የሚያሳስቱ ጉዳዮች ወይም ወንጀል በመሥራት ስምምነቱን ጥሶ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታዎች እየተመለከቱ ስለመሆኑ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሰው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የፍትህ ሚኒስቴሩ ቦይንግ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደሩን ለማጭበርበር ከመሞከሩ ጋር የቀረበበት ክስ ይቀጥል ወይም ይሰረዝ በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ለስድስት ወራት ቀነ ገደብ የተሰጠው ሲሆን፣ ይህም ሰኔ 30/2016 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ።

በዚህም ወቅት የአላስካውን የአየር መንገድ ክስተት በመርመር ቀጣዩን እርምጃ የሚወስን መሆኑንም ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቅርብ ሰው መናገራቸውን ሮይተርስ አስነብቧል።

መጋቢት 01/2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ናይሮቢ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር አሰቃቂው አደጋ የደረሰው።

በዚህ አደጋ ከ35 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ የ157 ሰዎችን ሕይወት ተቀጥፏል።

በ737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሱት የኢትዮጵያው አየር መንገድ እና የኢንዶኔዢያ ላየን ኤር አውሮፕላን አደጋዎችን ተከትሎ ቦይንግ የአብራሪዎቹን አቅም ጥያቄ ውስጥ በማስገባት እና ጥፋቱን ወደ ሌሎች በማዛወር ትችት ሲቀርብበት ነበር።

ከአምስት ዓመት ገደማ በፊት ለደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737-ማክስ 8 አደጋ ምክንያት የቦይንግ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት (ኤምካስ) ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

በሪፖርቱም መሠረት ለአውሮፕላኑ አደጋ ምክንያት ቦይንግ የገጠመው ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም) የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ችግር እንደሆነም ገልጿል።

ቦይንግ 737- ማክስ- 8 ለሁለት የአውሮፕላን አደጋዎች እና ለበርካታ ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑን ተከትሎ በዓለም ላይ ያሉ አውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ እግድ ተጥሎበት ነበር።

በቦይንግ አስፈላጊው ማስተካካያ ተደርጎ ተገቢው ምርመራ እና ሙከራ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለት ዓመት በፊት አውሮፕላኑን ወደ አገልግሎት መመለሱን መግለጹ አይዘነጋም።