እታገኘሁ መኮነን
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) ህዳር07/2016“ በአማራ ክልል እየጨመረ የመጣው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ኢሰመጉን በእጅጉ ያሳስቡታል! ” በሚል ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ግጭት ዘላቂ የሆነ በቂ መፍትሔ ባለመሰጠቱ ምክንያት ከፍተኛ የሆኑ የሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ይገኛሉ ብሏል፡፡
ኢሰመጉ በአማራ ክልል ውስጥ ያለውን ግጭት አስመልክቶ ለግጭቱ መነሻ የሆኑ ምክንያቶች መታየት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት ይህ አለመግባባት ለከፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት እንዳይሆን ሲያሳስብ እና ሲወተውት ቢቆይም ከመንግስት በኩል ለኢሰመጉ ምክረ ኃሳቦች በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ እና ለግጭቱ ዘላቂ መፍትሔ ባለመቅረቡ ምክንያት መጠነ ሰፊ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በክልሉ እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል ብሏል፡፡
በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በግጭቱ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች ላይ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ ማፈናቀል፣ ጾታዊ ጥቃት እና ከፍተኛ የሆነ የንብረት ውድመት መከሰቱን እንዳረጋገጠም ጠቅሷል፡፡
መንግስት ድሮዎኖችን ጨምሮ ከባድ መሳሪያዎችን ተጠቅሞ ንፁሀንን ገድሏል
በግጭቱ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን ይህም የተፈጸመው በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በታጠቁ ቡድኖች መሆኑን የጠቀሰው የኢሰመጉ መግለጫ በእዚህ ግጭት ላይ ድሮኖችን ጨምሮ ከባድ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል በእነዚህም መሳሪያዎች በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ኢላማ ተደርገዋል ብሏል፡፡
በእዚህ ግጭት ምክንያት ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃቶች መፈጸሙን እና ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች በቂ የሆነ የህክምና እና የስነልቦና ድጋፍ እንዳላገኙም ጠቅሷል ፡፡ በተጨማሪም በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን እና በተደጋጋሚ በሚዘጉ መንገዶች እና በሌሎች ምክንያቶች ምክንያት ለተፈናቃዮች በቂ ድጋፍ ለማቅረብ እንዳልተቻለ አትቷል፡፡
ኢሰመጉ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያደርጉ፣ በክልሉ በግጭቱ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ አካላት በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸውን ሰዎችና ንብረቶች ኢላማ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ በክልሉ ባለው ግጭት ውስጥ ተሳትፎ በሌላቸው አካላት ላይ ጥቃት የፈጸሙ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ታጣቂ ቡድኖች ላይ ተገቢውን ምርመራ በማድረግ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ በክልሉ ባለው ግጭት ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች ተገቢ የሆነ የህክምና እና የስነልቦና ድጋፍ በአፋጣኝ እንዲሰጥ እና ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮችም ተገቢ የሆነ አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሰጥ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
