የባህር ሀይል ወታደሮች በአማራ ክልል ውጊያ እየተሳተፉ መሆኑን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ገለጸ::

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ  “የኢትዮጵያ ባህር ሀይል ማሪን ኮማንዶ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ተሰማርቷል” ብሏል።

ተቋሙ የባህር ሀይል ዋና አዛዥ ተወካይ ሬር አድሚራል ናስር አባዲጋን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው “ጽንፈኛ” ባላቸው ቡድን አባላት ላይ እርምጃ እንደወሰደ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ባህር ሀይል የባህር ሃይል ኮማንዶዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ባሉ ወረዳዎች እንደተሰማሩ እና ግዳጃቸውን እየተወጡ እንደሆነም አዛዡ መናገራቸው ተገልጿል። የባህር ሃይል ኮማንዶ በመርከብ ላይ በባህር ከሚሰጠው ተልዕኮ በተጨማሪ በማንኛውም ጊዜ ግዳጁን የሚወጣ ሀይል እንደሆነም ሬር አድሚራል ናስር አባድጋ ተናግረዋል ተብሏል።

የባህር ሃይል ኮማንዶ ከአማራ ክልል የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን በወሰዳቸው እርምጃዎች የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱንም በዚሁ ዘገባ ላይ ተጠቅሷል።

የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን “መልሼ አደራጃለሁ” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የ”ፋኖ” ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን ይህ አዋጅ ሊጠናቀቅ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል።

የፍትህ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቲየስ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት በአማራ ክልል ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄደው ውጊያ ንጹሀን ዜጎች ከጥቃት እየተጠበቁ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ተመድን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርት ላይ ጠቅሰዋል።

ለአብነትም በባህር ዳር፣ መራዊ፣ ማጀቴ እና ሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት ንጹሀንን ሆን ብለው እንደገደሉ ተቋማቱ በሪፖርቶቻቸው ላይ የተገለጸ ሲሆን የፌደራል መንግሥት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን ውድቅ አድርጓል።