የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ከመንግስት ጋር በማበር” ፓርቲውን ለማፍረስ ሞከሯል የሚል ክስ አቀረበ

ሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ (ሲፌፓ) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በፓርቲው የቀድሞ አባላት ላይ ክስ መስርቻለሁ አለ፡፡ፓርቲው ክስ የመሰረተው “ቦርዱ የፓርቲው ውስጠ-ጉዳይ ላይ ጠልቃ በመግባት” እንዲሁም ከፓርቲው ከተሰናበቱት የቀድሞ አባላት ጋር በማበር የሀገሪቱን ህግና የኢፌዴሪ ህገመንግስት በተፃረረ መልኩ የተለያዩ “ህገወጥና አደገኛ ውሳኔ” በማስተላለፋቸው ነው ብሏል፡፡

ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን ለማፍረስ ከመንግስት ተልዕኮ ወስደው የፓርቲውን ህልውና ለአደጋ በማጋለጣቸው ምክንያት ከፓርቲው የተሰናበቱ አባላት ጋር ተባብሯል ሲል ከሷል።

እንዲሁም ፓርቲው ከዚህ በፊት በዲሲፕሊን ጥሰት ምክንያት ከፓርቲው የተሰናበቱ ግለሰቦች የፓርቲውን ንብረትና መስሪያ ቤት አስረክበው በስርዓት መውጣት ሲገባቸው “ከመንግስት ተልዕኮ በመቀበልና በቦርዱ አጋዥነት ለቀው ባለመውጣታቸውና በፓርቲው ስም የተለያዩ ህገወጥ እንቅስቃሴ” እያደረጉ ይገኛሉ በተባሉት ጴጥሮስ ዱቢሶ፣ ቦርሳሞ ቦሮጄ እናማቴዎስ ካኑ ላይ ክስ መመስረቱን ገልጿል።

ከዚህ ቀደም የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ጴጥሮስ ዱቢሶ እና ግብረ አበሮቻቸው  ፓርቲውን ከውስጥ ለማፍረስ ሲሰሩ ተጨባጭ ማስረጃ በመገኘቱ  የዲስፕሊን እርምጃ በመውሰድ ከአባልነት አግደናቸዋል ብሏል ፓርቲው፡፡

ሲፌፓ በተወሰደው የዲሲፕሊን እርምጃ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተከሳሾች የቀረበለትን አቤቱታ ለመሻር የሄደበት አካሄድ “አደገኛ” በመሆኑ በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል ሲል የካቲት 11 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ አሳስቦ ነበር።

በተመሳሳይም ከዚህ ቀደም  የሲዳማ ፈደራሊስት ፓርቲ “ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በመንግስት አካላት የተቀናጀ ፓርቲውን የማፍረስ ሴራ” ምክንያት ከአገራዊ ምክክሩ ሊወጣ እንደሚችል  አሳውቆ ነበር፡፡

“በአጠቃላይ እየደረሰብን ያለው እስር፣ አፈና፣ ስደት፣ ሁከት፣ እንዲሁም ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የመንግስት አካላት የተቀናጀ ፓርቲውን የማፍረስ ሴራ በሀገራዊ ምክክር የለውጥ ተስፋ እንዲንቆርጥ አድርጎናል” ሲል ገልጾም ነበር።

የፌደራል ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ክሱን ለመስማት ለ ግንቦት 12 ቀን 2016 ልደታ ምድብ ችሎት አንደኛ ምርጫ ፍትሃብሔር ቀጥታ ክስ ችሎት እንዲቀርብ  ለምርጫቦርድ ደብዳቤ ልኳል።