ሕወሓት ብልፅግናን ለመቀላቀል በድርድር ላይ ነው

ሕወሓት ከአራት ዓመት በፊት “ሕገ – ወጥ ነው” ያለውን ገዥውን ፓርቲ ብልፅግና ለመቀላቀል ተከታታይ ድርድሮች እያደረገ መሆኑን  ከተለያዩ ምንጮች መረጃ አግኝቻለሁ በማለት ዋዜማ ዘግቧል፡፡

ከሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የፈረመው ሕወሓት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በሊቀመንበርነት የሚመሩትን ብልፅግናን በመቀላቀል በሀገራዊ ጉዳዮች አብሮ ለመስራት መስማማቱን ቢገልፅም ፓርቲውን ለመቀላቀል ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል ብሏል ዋዜማ በዘገባው።


ከብልፅግና በፊት የነበረው ኢሕአዴግ እኩል የስራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ውክልና ያላቸው አራት ንዑስ ፓርቲዎች ጥምረት ሲሆን ብልፅግና ግን አንድ ወጥ ፓርቲ ነው። የብልፅግና የፓርቲ ውክልና በህዝብ ብዛት የሚወሰን እንጂ እንደ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እኩል ውክልና አይኖራቸውም።


አሁን እየተደረገ ባለው ድርድር ሕወሓት የብልፅግና ፓርቲ ሕገ-ደንብ ተሻሽሎ በፓርቲ ውስጥ አባል ድርጅቶች እኩል የማዕከላዊ ኮሚቴና የስራ አስፈፃሚ ውክልና እንዲኖራቸው ይፈልጋል ተብሏል። ብልፅግና ግን ሕወሓት የተናጠል ህልውናውን አክስሞ ብልፅግናን እንዲቀላቀልና ውክልናውም በትግራይ ህዝብ ቁጥር ልክ የሚወሰን መሆኑን ይገልፃል ይላል ዘገባው።


የሕወሓት ሊቀ መንበር ደብረፅዮን ገብረሚካዔል በአዲስ አበባ ተገኝተው ይህን ድርድር የጀመሩት ሲሆን ከሁለት ሳምንት በኋላ የብልፅግና ምክትል ሊቀመንበር አደም ፋራህ ወደ መቀሌ ተጉዘው በጉዳዩ ላይ በስፋት መነጋገራቸውም ተጠቅሷል።


በሕወሐት በኩል ብልፅግናን መቀላቀል “ስህተት ነው …አስፈላጊም አይደለም” ብለው የሚያምኑ አመራሮች ቢኖሩም፣ ውህደቱ ለትግራይ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ጠቀሜታ አለው፣ በተለይም የትግራይን ፀጥታና ደህንነት ለመስጠበቅ ከብልፅግና ጋር አብሮ መቆም አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑም አሉ።

 ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕወሃት፣ በውህደት ዙሪያ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ውይይት እያደረገ ስለመኾኑ የተሠራጨው ዘገባ “ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው” በማለት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስተባብሏል። ሕወሃት፣ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጋር ባሁኑ ወቅት እያደረገው ያለው ንግግር፣ በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት መሠረት የሰፈነውን ሰላም በማስፋትና በማጠናከር ዙሪያ ብቻ እንደሆነ ገልጧል። በሕወሃትና በገዥው ፓርቲ መካከል በርዕዮተ ዓለም እና በዓላማ ረገድ መሠረታዊ ልዩነቶች እንዳሉ የገለጠው የሕወሃት መግለጫ፣  ሁለቱ ፓርቲዎች የሚወያዩባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ ብሏል።