የምክክር ኮሚሽኑ በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እና በስድስት ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታ መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

ባለፉት 4 ወራት አዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በ6 ክልሎች የሃገራዊ ምክክር የተሳታፊዎች ልየታ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ የ4 ወራት አፈጻጸም ረፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት ያካሄደ ሲሆን  የኢትዮጵያ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን የ4 ወራት አፈጻጸም ሪፖርትንም አዳምጧል፡፡

ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ በቅድመ ዝግጅት ስራው ከእድሮች፣ ከሃማኖት ተቋማት፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከመምህራን ማህበር ጋር በአጋርነት እየሰራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በመላ ሃገሪቱ እየተካሄደ ባለው የተሳታፊዎች ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር ሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች ጨምሮ በ6 ክልሎች  ላይ በተለይ የልየታ ስራው መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡

በኮሚሽኑ ዕቅድ መሰረት እስካሁን በሁሉም ክልሎች የተሳታፊ ልየታውን ማከናውን ይቻል ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ በአንዳንድ ክልሎች ባለው የጸጥታ ሁኔታ ማከናወን እንዳልተቻለ አንስተዋል፡፡ ለዚህ መፍትሄ ሁሉም አካላት በውይይት ማመንን  እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሃገራዊ ምክክሩ በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ 1ሺ 400 ወረዳዎች ሁሉም ህብረተሰብ በተወካዮቻቸው አማካይነት ተሳታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል ያሉት ኮሚሽነሩ ይህንንም ለማሳካት በትጋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከተሳታፊ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ጋር በተገናኘ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄና አስተያየት የቀረበ ሲሆን ከኢትዮጵያ ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ ያደረገውን የዘላቂ ሰላምና መግባባት የመፍጠር ተልዕኮ ለማሳካት ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለው ስራ አበረታች ነው ያሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለበለጠ ውጤታማነት የሁሉንም ዜጎች የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል፡፡