ኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሳዑዲ አረቢያ የአፍሪካ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ወደሪያድ አቅንተዋል። የአገሪቱ የመረጃ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው እንዳሰፈሩት ኢሳያስ ዛሬ ማለዳ ላይ ወደ ሳዑዲ አምርተዋል። አብረዋቸው ከተጓዙ የልዑካን ቡድናቸው አባላት መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ኦስማን ሳለህ፥ የፓርቲያቸው የምጣኔ ኃብት ጉዳዮች ኃላፊ ሃጎስ ገብረህይወት እንዲሁም የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ነስረዲን ቤኪት ይገኙበታል።
በጉባዔው ይታደማሉ ተብሎ ከሚጠበቁ ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች መካከልም የኬንያው ዊሊያም ሩቶ እና የናይጄሪያው ቦላ ቲኑቡ ይገኙበታል።
የሳዑዲ አረቢያ የአፍሪካ ጉባዔ ሪያድ ከተለያዩ የአህጉሪቷ አገራት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረትን ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት የምታጠናክርበት ነው። ጉባኤው ተፋፍሞ የቀጠለው የጋዛ ቀውስ ጥላ ያጠላበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ በቀውሱ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ሊተላለፍ እንደሚችል ተዘግቦም ነበር። ሪያድ የሳዑዲ የልማት ፈንድ እና የእስላማዊ የልማት ባንክ በመሳሰሉ ተቋማት በአፍሪካ አገራት ላይ ያላትን ተፅዕኖ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከፍ አድርጋለች።
