አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ እና ጤና ጥናት በሚቀጥሉት 3 ዓመታት ውስጥ ይካሄዳል ተባለ ::

በአሸናፊ አሰበ

የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት በየአምስት አመቱ የሚካሄድ ሲሆን አራተኛው ጥናት እ.አ.አ በ2016 ከወጣ በኋላ ሳይወጣ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በበኩሉ አምስተኛው ዙር የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት በኮቪድ እና ሌሎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች መሰራት ከነበረበት ጊዜ በሁለት ዓመት መጓተቱን ገልጾ በተያዘው በጀት ዓመት መጋቢት ወር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት አቅዶ እየተንቀሳቀስ እንደሆነ የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ እና የመረጃ ስርጭት ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ ለአዲስ ጊዜ ገልጸዋል።

ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም በሚቆየው የስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም ትግበራ ወቅት በሚካሄዱት ቆጠራዎችና ጥናቶችን በሚመለከት ሲከናወኑ በነበሩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ እና የተቀናጀ የቤተሰብ ፍጆታ ጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ለማድረግ መታቀዱን አገልግሎቱ በማሕበራዊ ትስስር ገጹ አጋርቷል።

የመጀመሪያው የሆነው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ከትልልቅ ድርጅቶች እስከ መንገድ ላይ እስካሉ የኢኮኖሚ ተቋማት በቆጠራው እንደሚካተቱ ያነሱት ሃላፊው ከኢንዱስትሪ ሚኒስትር ጋር በጋራ እንደሚሰራ እና ለኢንዱስትሪ ፖሊሲ ቀረፃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል ሲሉ ሃላፊው ጨምረው ለአዲስ ጊዜ ገልጸዋል።

ሁለተኛ ዙር የግብርና ቆጠራ፣ በቀጣይ ሶስት ዓመታት የስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም ትግበራ ወቅት እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን የመጀመሪያው በ2004 ተካሂዶ እንደነበር እና ከሌሎች ጥናቶች ለየት ባለመልኩ አመቱን ሙሉ የሚሰራ ጥናት እንደሆነ ሃላፊው ገልጸው የተቀናጀ የቤተሰብ ፍጆታ ጥናትም ዕለታዊ ፍጆታዎችን ለመገምገም ታቅዶ የሚጀመር ጥናት ሲሆን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግ እንደሆነ ሃላፊው አስታውቀዋል።

ሁሉንም ጥናቶች በ2017 ዓ.ም ለመጀመር ታቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን እና በ 2018 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙን አቶ ሳፊ ገመዳ ለአዲስ ጊዜ ገልጸዋል።