ጋዜጠኞች ለሚያጋጥማቸው የመብት ጥሰት ጥብቅና የሚቆም እና የህግ ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጥ የጋዜጠኞች  እና የሕግ ባለሙያዎች ጥምረት ሊመሰረት ነው፡፡

እታገኘሁ መኮነን

MELA ( Media Lawyers alliance )ተብሎ የተሰየመው ይህ የሚዲያ እና የህግ ባለሞያዎች ጥምረት በምስረታ ሂደት ላይ መሆኑን ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድኅ) ሰምተናል፡፡ ኅብረቱ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ጋር በመሆን  በጥምረቱ ዙሪያ  ትናንት ማክሰኞ ነሀሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ውይይት አዘጋጅቶ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድኅ)  ዳሬክተር አቶ መስዑድ ገበየሁ ጥምረቱ  የጋዜጠኝነት ሙያ ማህበራትን ማገዝ፣ጋዜጠኞች በሰሩት ስራ ለሚያጋጥማቸው የመብት ጥሰት እና ጫና የሕግ ድጋፍ የመሰጠት፣ለጋዜጠኞች መታሰር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር የማድረግ፣ በመገናኛ ብዙኃን ዙሪያ  ህጎች ሲወጡ በባለሞያዎች ጥናት ማስጠናት እና ግብዓት ማቅረብ እንዲሁም በሚዲያው ህብረተሰብ ውስት ያለውን የህግ ግንዛቤ ክፍተትን ለመሙላት የሚያስችሉ ስልጠናዎችን መስጠት ዓላማው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሙያ ማኅበራት በተለይም ጋዜጠኞች የማይመች ምኅዳር ውስጥ እያለፉ መሆናቸው፣ የጥምረቱ አመሠራረት ላይ በነበረ ውይይት የተነሳ ሲሆን፣ ጥምረቱ ሙያው የሚደርስበትን ጫና በእጅጉ ይቀንሳል ተብሏል፡፡

የሚዲያ ባለሙያዎችን የሚደግፍ የሕግ ባለሙያዎች መኖሩ ለዘርፉ የአማካሪነትና የጠበቃነት ሚና በመጫወት፣ በሕግና የሕግ ዙሪያ የሚፈጠሩ የሚዲያ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ድጋፍ በመስጠት፣ በአገሪቱ በዴሞክራሲ ግንባታ ሒደት ሚዲያውና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከፍ ያለ ሚና እንዲጫወቱ እንደሚያደርግ፣  የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድኅ) ዋና ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዩኔስኮ ተወካይ አቶ አደራው ገነቱ በበኩላቸው፣ የጥምረቱ መመስረት ለመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች እና አጠቃላይ ለሚዲያው ምህዳር ትልቅ አስተዋፅዖ ኖረዋል ብለዋል፡፡ዩኔስኮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች እንዲጠበቁ በሚያደርገው ድጋፍ፣ ጥምረቱ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲጠናከሩ የማድረግ ሚናም ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ2020 ጀምሮ ሁለት ጋዜጠኞች መገደላቸውን፣  200 ጋዜጠኖች መታሰራቸውን እንዲሁም  54 ጋዜጠኞች ደግሞ ሃገር ጥለው መሰደዳቸውን በመግለጽ ጋዜጠኞች ለሚያጋትማቸው እስር እንግልት እና የመብት ጥሰት የሚቆም አካል ቢኖር ይህ አይሆንም ነበር ብለዋል፡፡

በጥምረቱ ውስጥ እነማን ይሳተፉ፣ ጥምረቱ የሕግ አገልግሎት የሚሰጠው ለእነማን እና በምን  መስፈርት ነው የሚሉት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ወደፊት ውይይት ተደርጎ እንደሚወሰንም ተነግሯል፡፡

ጥምረቱን ለመመስረት የሚያስችሉ ሂደቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን የገለፁት የኢሰመድኅ ዳሬክተር አቶ መስዑድ ሂደቱ ሲጠናቀቅ እና ጥምረቱ ወደ ስራ ሲገባ በሚዲያ ህግ ዙሪያ በቂ ዕውቀት እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ጋዜጠኞች ጥብቅና የሚቆም ይሆናል ብለዋል፡፡