ማህበሩ የጋዜጠኞቹ የፍርድ ሂደትም ከፖለቲካ አተያይ በፀዳ መንገድ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር አዲስ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በአዲስ አበባ ቃሊቲና ቂሊንጦ ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን መጎብኘታቸውን ትናንት ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል፡፡
በጉብኝታቸውም ስለ ማረሚያ ቤት አያያዝ እና አጠቃላይ የፍትህ ሂደቱ ያለበትን ሁኔታ ከጋዜጠኞቹ ጋር እንደተወያዩ ማህበሩ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር በተያዙበት ወቅት የተያዙበት መንገድም ሆነ ከተያዙ በኃላ ያለው የፍርድ ቤት ሂደት አግባብነት እንደሚጎድለው ተናግረዋል፡፡
በሁለቱም ማረሚያ ቤቶች ከሁለት ዓመት በላይ ሳይፈረድባቸው የታሰሩ ጋዜጠኞች መኖራቸውን ማኅበሩ እንዳረጋገጠ አስታውቋል።
ስለሆነም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ እንዲሁም የሚዲያ ምህዳሩ ነፃ እንዲሆን የሚመለከታቸወን አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማህበሩ ጠይቋል።
የማህበሩ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ተቀዛቅዞ የቆየውን የማኅበሩን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለማስቀጠል አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ለመንቀሳቀስም ውይይት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ተቀዛቅዞ የቆየውን የአባላት ተሳትፎ ለማሳደግ ነባር አባላትን ማነቃቃት እና የአዳዲስ አባላትን ምዝገባ እንደ አዲስ ጀምሯል።
ከአባላት ማፍራት እና ማነቃቃት በተጨማሪ ማኅበሩ ከዚህ ቀደም በንቃት ይሰራቸው የነበሩና ለሙያው ማደግ ሚና ያላቸውን ተግባራትንም ለማከናወን ዕቅድ ይዞ ወደ ተግባር ገብቻለሁ ብሏል።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር በዋነኛነት የጋዜጠኞችን መብትና ክብር ለማስጠበቅ በሚል የተቋቋመ የሙያ ማህበር ነው።
ሙያው ከአገራችን የፖለቲካ ምስቅልቅል ሁኔታ ጋር አብሮ ፈተና ውስጥ የገባ መሆኑ የሚታወቅ ነው ያለው ማህበሩ ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ የፈጠራቸው የጋዜጠኞች አስር ፣ ስደትና ውክብያ የወቅቱ የባለሙያው ትልቅ ፈተና መሆኑን ገልጿል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር ችግር ላይ የወደቀውን የጋዜጠኞችን ደህንነትና ሙያዊ ነፃነት ለማስከበር እንደሚሰራ አስታውቋል።
ከዚህ ጋር አያይዞም ማኅበሩ በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች አባል ሁነው እንዲመዘገቡና ማህበሩን በማጠናከር ለሙያው መከበር ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ድምፅ እንዲሆኑ ጥሪውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጋዜጠኞች በሰሩት የሚዲያ ዘገባ በህግ የሚጠየቁ ቢሆን እንኳ በቁጥጥር ስር ሳይውሉ ወይም ሳይታሰሩ ጉዳያቸውን በውጭ መከታተል እንደሚችሉ ደንግጓል፡፡ ሆኖም አዋጁን ባላከበረ መልኩ በኢትዮጵያ በተለያዩ ማረሚያ ቤቶች በርካታ ጋዜጠኞች ታስረዋል፡፡
