በሚቀጥሉት 20 ቀናት በሚጥለው ከባድ ዝናብ የተነሳ ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና የወንዞች ሙላት ሊያጋጥም ይችላል ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስጠነቀቀ።
በሚቀጥሉት 10 ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት በዓባይ፣ ተከዜ፣ ባሮአኮቦ፣ ኦሞ፣ ጊቤ፣ አዋሽ፣ አፋር ደናክል፣ የላይኛውና የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው የገናሌ ዳዋና ዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች መካከለኛና በጣም ከፍተኛ እርጥበት እንደሚኖራቸው ጠቁሟል።
ተዳፋታማ በሆኑ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተትና መሰንጠቅ፣ እንዲሁም የሰብል በጎርፍ የመጠረግ ሁኔታዎች እንዳይኖር መጠንቀቅ ያስፈልጋል ሲል ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።
እርጥበት በሚበዛባቸው አካባቢዎችም የሰብል በሽታ እንዳይከሰት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም ጠቁሟል።
በተጨማሪም በሚቀጥሉት 8 ቀናት በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በሰሜን ምስራቅ እና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች አልፎ አልፎ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያስከትል ከባድ ዝናብ እንደሚኖር ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው አካትቷል።
አልፎ አልፎ በሚፈጠረው ጠንካራ የሆነ የደመና ክምችት ምክንያት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በረዶና ነጎድጓድ የቀላቀለ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይከሰታል ያለው መግለጫው አስፈላጊው የቅድመ ጥንቃቄ ስራ እንዲከናወን አሳስቧል።
ወደ ግድቦች የሚገባው ውሃ ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳም አሁናዊ የውሃ ከፍታቸው አስጊ በሆነባቸው እንደ ፊንጫ፣ ጣና በለስ፣ ከሰምና ርብ የመሳሰሉት የኃይል ማመንጫ እና የመስኖ ግድቦች ላይ የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው አሳስቧል።
