የቅድመ መደበኛ ስርዓተ ትምህርት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት ይፋ ሆነ

ችልድረን ብሊቭ  ህጻናትን፣ ቤተሰቦችን እና ማህበረሰብን  በአለም አቀፍ ደረጃ ለማብቃት የሚሰራ  አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ድርጅቱ ድህነትን እና ኢፍትሃዊነትን በማሸነፍ ላይ ያተኮረ ተልእኮ በመያዝ፣ በትምህርት ቤት ውስጥ  ህፃናት ፣ በራስ መተማመንን እና የራሳቸውን የወደፊት ህይወት ለመቅረጽ የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ይሰራል፡፡ችልድረን ብሊቭ  የቻይልድ ፈንድ አሊያንስ አባል ነው፡፡ ቻይልድ ፈንድ በ70 ሃገራት  ወደ 36 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናትን እና ቤተሰቦቻቸውን በጋራ የሚደግፍ ዓለም አቀፍ ኔትወርክ ነው፡፡

ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረው ድርጅቱ  እንደ ቅድመ ልጅነት እንክብካቤ እና ልማት ፣ የእናቶች እና ህጻናት ጤና እና ስነ-ምግብ ፣  የወጣቶች ስራ ስምሪት ላይ እየሰራ ያለ ተቋም ነው፡፡  

እ.ኤ.አ. በ 2023 የበጀት ዓመት ፣  ችልድረን ብሊቭ  በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ከ283,000 በላይ ተጋላጭ ህጻናትን፣ ወጣቶችን፣ ሴቶችን እና ወንዶችን  ለማህበረሰቡ ባለቤትነት በተነደፉ ሁለንተናዊ የማህበረሰብ ልማት ፕሮግራሞች ላይ እንዲሳተፉ ሰፊ ስራ ሰርቷል፡፡

ተቋሙ ቢዚህ ሳምንት  ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ወጣት ህይወት እና ሌሎች ሀገር አቀፍ እና አለምአቀፍ አጋሮች ከተውጣጡ ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር የቅድመ ህፃናት እንክብካቤ እና ትምህርትን (ኢ.ሲ.ሲ.ኢ.) ከኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍ ጋር በማዋሃድ ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን ይፋ አድርጓል።

ጥናቱን ካጠኑት ባለሞያዎች መሃል አንዱ የሆኑት የኦል አባውት ችልድረን ሃገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር እና ተመራማሪ ፍስሃ ተክሉ የምርምር ግኝቶቹ በቅድመመደበኛ ትምህርት ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ናቸው ብለዋል፡፡

የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው  የቅድመ መደበኛ ትምህርት በአካዳሚክ ዕዉቀት  ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉ በህፃናቱ ማህበራዊ እና አዕምሮአዊ እድገት ላይ ተፅእኖ አሳድሯል ተብሏል።

በመሆኑም የትምህርት ስርአቱ ውስጥ  ሀገር በቀል ጨዋታዎችን ማካተት እና ማስተማር ክህሎቱን  ለማጎልበት እንደሚረዳም  በጥናቱ ተጠቁሟል።

በቅድመ መደበኛ ትምህርት አገልግሎት  ላይ ከመምህራን እጥረት አንስቶ  የስልጠና እንዲሁም ለመማር ማስተማሩ የሚረዱ  ግብአቶች  በበቂ ሁኔታ ያለመኖር ሌላው ክፍተት መሆኑ ተገልጿል።

በመሆኑም ብሄራዊ የትምህርት ፖሊሲዉ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ይዘቶች ላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባው ተጠቁሟል።

 ይህንን ጥናት በትምህርት ፖሊሲው ላይ ማካተት እና ከቅድመ ሕጻናት ትምህርት ጋር በተገናኘ ከ30-40 በመቶ ለውጥ ማምጣት ዓላማቸው እንደሆነም ተናግረዋል።

የችልድረን ብሊቭ ዋና ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ሰለሞን እና የኢትዮጵያ ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ አቶ አባይ ገና በግኝቶቹ ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልፀው፣ “ጥናቱን  በኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ ውስጥ ማዋሃድ በልጆች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ ልማት ቁርጠኛ መሆን ነው ብለዋል። በልጅነት ጊዜ ጠንካራ መሰረት በመጣል ለሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የበለፀገ የወደፊት ዕድል መንገድ እንከፍታለንም ብለዋል፡፡