ኢትዮጵያ ለቴሌቪዥን ስርጭት በዓመት 7 ሚሊዮን ዶላር እየከፈለች ነው ተባለ

የቴሌቪዥን ባለንብረቶች ለሳተላይት ስርጭት የምንከፍለው ዋጋ ጭማሪ አሳስቦናል አሉ፡፡ በዓመት 7 ሚሊዮን ዶላር እየከፈሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባለንብረቶች ማህበር በየዓመቱ የሳተላይት ስርጭት የሚከለው ዋጋ ውድነት አሳስቧት ነበር አባላቱ ወደ ኢትዮሳት እንዲገቡ ያደረገው፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም ለእነዚህ የቴሌቭዥን ባለንብረቶች  ስርጭታችሁን በኢትዮ ሳት በኩል ብታደርጉ በየዓመቱ ለሳተላይት የምትከፍሉት ክፍያ ይቀንስላችኋል ብሎ ማበረታቻ ሰጥቶ ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ ሰባ የሚሆኑ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች  ስርጭታቸውን በኢትዮሳት በኩል ያደረጉ ሲሆን ዓመታዊ ወጪያቸው ግን እንዳልቀነሰላቸው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ብሮድካስተሮች ጉባኤ ላይ እንደተገለጸው ወጪ ለመቀነስ ብለው ወደ ኢትዮሳት የገቡ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በዓመት ለሳተላይት ስርጭት 7 ሚሊዮን ዶላር እየከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ቤተልሄም ንጉሴ ግን  የኢትዮ-ሳት አገልግሎት ኢትዮጵያ ለሳተላይት የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ መቀነሱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ የኮሙኒኬሽን ሳተላይት ባለቤት ለመሆን እየሰራች ስለመሆኑም ምክትል ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ ኢድሪስ፤ በኢትዮሳት አሁን ላይ ከ70 በላይ የኃይማኖት፣ የንግድ፣ የህዝብና ሌሎች የሀገር ውስጥ ቻናሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮ ሳት አገልግሎትም 17 ሚሊዮን ቤቶች ላይ መድረሱን ገልጸው ይህም ከተደራሽነት አንጻር ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

የዓለም አቀፉ የሳተላይት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አቅራቢ (SES) የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የምስራቅ አፍሪካ የሽያጭ ሃላፊ መነን አገኘሁ፤ በኢትዮጵያ ከ18 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቲቪ ተጠቃሚዎች መካከል 17 ሚሊዮኑ በኢትዮ-ሳት ስርጭት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2017 ከነበረው ቴሌቪዥን ተጠቃሚ አንጻር አሁን ላይ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው የኢት-ሳት ተደራሽነትም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።