ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ ከአገር ለመሰደድ መገደዱን ተናገረ

ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ በዋዜማ ሬዲዮ፣ ኢኤምኤስ እና ሌሎችም ሚዲያዎች በጋዜጠኝነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ ሸገር ከተማ “ሕገ ወጥ ግንባታ” ናቸው ተብለው በፈረሱ ወደ 100 ሺህ የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችና በተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ለዘገባ ወደ ስፍራው ባመራበት ወቅት በፖሊስ ተይዞ ለእስር ተዳርጎም ነበር፡፡

በዚህ ወቅት በፖሊስ ድብደባ፣ እስርና ማዋከብ ደርሶበት እንደነበር የተናገረው ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ በዋስ ከእስር ቤት ወጥቶ እንዲከራከር በፍርድ ቤት ተወስኖለት ቢወጣም ዛቻና ማስፈራሪ ሲደርስበት እንደነበረ ነግሮኛል ሲል ኢትዮ ነጋሪ አስነብቧል፡፡

በቅርቡም ለዋዜማ ሬድዮ እና ኢንተር ኒውስ ዘገባ ለመስራት ወደ አማራ ክልል ደሴና ሐይቅ ከተሞች በተጓዘበት ወቅት በክልሉ ኮማንድ ፖስት ታስሮ እንደነበረም አክሏል።

አስቀድሞ በታሰረበት ጉዳይ ለዋስትና የተያዘውን ገንዘብ ለማስለቀቅ ሸገር ከተማ በተገኘ ወቅት ፖሊስ ይዞት እንደነበረ እና በተጨማሪም ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ VOA ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ጉዳይ ፌደራል ፖሊስ ለጥያቄ ትፈጋለህ ብለው አስገድደው ወስደውት እንደነበረ የገለጸው ጋዜጠኛው በደረሰበት ተደጋጋሚ ጫና ምክኒያት አገር ለቆ መውጣቱን ኢትዮ ነጋሪ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ከተጽእኖ ነጻ ሆኜ የመስራት ፍላጎት ቢኖረኝም የመንግስት ተጽዕኖ ሊያሰራኝ ባለመቻሉ የምወዳት ሀገሬን ጥዬ ለመሰደድ ተገድጃለሁ ሲልም ጋዜጠኛ ሳሙኤል ተናግሯል ይላል የኢትየ ነጋሪ ዘገባ፡፡