የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካው አምባሳደር “ሳይጠየቁ ምክር” ሰጥተዋል ሲል ወቀሰ

በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ በቅርቡ በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ያሰሙት ንግግር “በደንብ ያልተጤነ” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቀሰ።

አምባሰደር ማሲንግ ከጥቂት ቀናት በፊት “ፖሊሲ ስፒች ኦን ሂዩማን ራይትስ ኤንድ ዳያሎግ” የተሰኘ ንግግር አሰምተው ነበር።

ማሲንጋ በንግግራቸው መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ፤ ያልተገደበ ሰብአዊ አቅርቦት እንዲኖር እና ለዚህም መነሻ የሚሆን ጊዜያዊ አገር አቀፍ የተኩስ አቁም አንዲደረግ አሳስበው ነበር።

ማሲንጋ  በንግግራቸው ሽፍቶች፣ ታጣቂ ቡድኖችና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በህይወት የመኖር እና የመከባበር መብቶች ላይ ጥሰት መፈፀማቸው የሕግ ሂደትንና የሕግ የበላይነት አለማክበርን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በጦርነት እና ግጭት ጊዜም ቢሆን “የሰብዓዊ መብት እና ሰብዓዊ ክብር” ሊረሱ አይገባም ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ በግጭት ወቅት “የሁሉም ዜጎች በተለይም የሰላማዊ ነዋሪዎች ደህንነት መጠበቅ አለበት” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐሙስ ባወጣው መግለጫ የአምባሳደሩ ንግግር “ብልኃት የሚጎድለው” ነው ይላል።

አምባሳደር ማሲንጋ በንግግራቸው የታጠቁ ኃይሎች “ከውይይት ይልቅ በሁከት ፖለቲካዊ ዓላማዎችን ለማሳካት መሞከራቸው በደሎች እንዲፈጸሙ በር ይከፍታል” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በመላ አገሪቱ ያሉ ሰላማዊ ዜጎች ከሕግ አግባብ ውጭ ግድያ፣ የዘፈቀደ እስራት፣ በግዳጅ መሰወር፣ ከግጭት ጋር የተያያዘ ጾታዊ ጥቃት እና ሌሎችም ጥቃቶች በተለያዩ ተዋናዮች እየተፈጸመባቸው መሆኑን የሚገልጹ ዘገባዎችን በማየታቸው ማዘናቸውንም ጠቅሰዋል።

ማሲንጋ እኒህ ችግሮች “እውነተኛ እና ግልጽ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን በመሳሰሉ መንገዶች በአስቸኳይ እና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ ሊፈቱ ይገባል” ብለዋል።

“የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ዳሬሰላም ድረስ በመጓዝ ችግሩን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ልባዊ ጥረት አድርጋችኋል። እጅ አትስጡ” በማለት በግጭቱ እየተሰቃየ ላለው ኅብረተሰብ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ፋኖን በተመለከተ ደግሞ “ለውይይት ዕድል መንፈጋችሁ የሚጠቅማችሁ እንዳልሆነ ልትረዱ ይገባል። እንደሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በቀጠለው ግጭት ምክንያት እየተሰቃዩ ያሉት ንጹሀን ዜጎች ናቸው። ብዙ የአማራ ተወላጆች ጥያቄያቸው ፍትሃዊ እንደሆነ ያምናሉ። ይህንን ደግሞ ማሳካት የሚቻለው በውይይት እንጂ በግጭት አይደለም” ብለዋል።

ህወሓት በበኩሉ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ መኖሪያቸው መመለስን ጨምሮ ሌሎችም እልባት ያላገኙ ጉዳዮችን በተመለከተ፤ “አካታች፣ ስርዓት እና የሰዎችን ክብር የጠበቀ” አካሄድ እንዲከተል አምባሳደር ማሲንጋ መክረዋል።

“ለውይይት ጊዜው አሁን ነው” ያሉት ማሲንጋ፤ ታጣቂ ቡድኖች ራሳቸውን ለውይይት እንዲያዘጋጁ መክረዋል። በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት “ፍጹም ባይሆንም” ሁሉም ወገኖች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው አበክረው አስገንዝበዋል።

የዋሺንግተን አምባሳደር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ እንዲህ ዓይነት ጠንከር ያለ አስተያየት ሲሰጡ መመልከት እምብዛም የተለመደ አይደለም።

አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን የእርስ በእርስ ጦርነት በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ከማድረግ ባለፈ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በዳሬሰላም በነበረው ድርድር በተለያየ ደረጃ ተሳታፊ መሆኗ ይታወቃል።

መግለጫው አክሎ አምባሳደር ማሲንጋ “ሳይጠየቁ” ለኢትዮጵያ መንግሥት ምክር ለመገለስ ሞክረዋል ሲል ወቅሶ “ያልተገባ ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቀርቧል” ብሏል።

ሚኒስቴሩ እንደሚለው በአዲስ አበባ የዋሺንግተን ተወካይ የሆኑት ማሲንጋ የሰጡት አስተያየት “ከሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ እና መልካም ወዳጅነት ጋር የሚቃረን” ነው።

“ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት፣ ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅና ዲሞክራሲን ማለምለምን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ናት ያለው መግለጫው ሚኒስቴሩ አዲስ አበባ ከሚገኘው የዩኤስ ኤምባሲ ጋር ተባብሮ መግለጫው ላይ የተንፀባረቁ ስኅተቶችና አለመጣጣሞችን ለማረምም ዝግጁ ነው ይላል፡፡