ህወሓት ኬሪያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገብረ እግዚብሔርን ከፓርቲ አባልነታቸው አሰናበተ

የካቲት 15/2016

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ትላንት ሐሙስ የካቲት 15፤ 2016 ባደረገው ስብሰባ ከከፍተኛ አመራሮቹ ውስጥ፤ ኬሪያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገብረ እግዚብሔርን ከማዕከላዊ ኮሚቴ እና ከፓርቲ አባልነታቸው ማሰናበቱን አስታወቀ። ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ እና ዶ/ር አብርሃ ተከስተ በፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡

ህወሓት በጦርነቱ ወቅት “በጠላት እጅ ወድቀው ነበር” ያላቸውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን  ያሰናበተው አስቀድሞ የነበሩትን ሁኔታዎች በመገምገም እና የፓርቲውን ህገ ደንብ በመከተል መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በዚህም መሰረት “እጃቸውን ለጠላት በመስጠት” እና “ምስጢር አሳልፈው በመስጠት” የተገመገሙት የቀድሞው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም እና የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉ ገብረ እግዚብሔር፤ ከማዕከላዊ ኮሚቴ እና ከፓርቲ አባልነታቸው መባረራቸውን አስታውቋል። የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት ኬሪያ፤ የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈፅም በመተባበር  እና በሀገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው የእስር መያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው 96 ሰዎች መካከል አንዷ ነበሩ። 

ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች አንዷ የነበሩት የፓርላማ አባሏ ሙሉ ገብረ እግዚያብሔር በቁጥጥር ስር የዋሉት ከኬሪያ መያዝ ከአንድ ወር በኋላ ነበር። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተጠርጣሪዎቹን የከሰሰው፤ በሕገ መንግስትና በሕገ መንግስት ስርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀልን እንዲሁም የሽብርተኝነት ድርጊቶች ፈጽመዋል በሚል ወንጀል ነበር። 

በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት፤ ዶ/ር ሰሎሞን ኪዳኔ፣ ዶ/ር ረዳኢ በርሄ፣ ወ/ሮ ኪሮስ ሃጎስ እና አቶ አጽብሃ አረጋዊ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ ተወስኗል፡፡ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በትላንቱ ስብሰባው፤ ህወሓት በቀጣይነት ለሚያካሄደውን 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ የሚሆኑ ሶስት አባላትን መርጧል። በኮሚቴው አባልነት የተመረጡት ወ/ሮ አልማዝ ገብረጻድቅ @ፈትለወርቅ ገብረእግዚያብሔር (ሞንጆሪኖ) እና አቶ ኢሳያስ ታደሰን ነው።