የካቲት 15/2016
ዘንድሮ የዘጠነኛው የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም ተረኛ አዘጋጅ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነበረች፡፡ፎረሙን የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ፣ የኢፌዲሪ ከተማና መሰረተ ልማት ሚስቴርና የወላይታ ሶዶ ከተማ አሰተዳደር በጋራ አሰናድተውታል፡፡
ለሰባት ተከታታይ ቀናት በቆየው በዚህ ዓውደ ርዕይ ላይ 124 ከተሞች በከተማ ልማት ዘርፍ ያከናወኗቸውን ተግባራት ለጎብኝዎች አስተዋውቀዋል፡፡ዓውደ ርዕዩ ከተሞች ልምድ የተለዋወጡበት፣ ሃሳባቸውን ያጋሩበት፣ የዕውቀት ሽግግር ያደረጉበት መድረክ ነበር፡፡
“የዘመኑ ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ዓውደ ርዕይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አማካኝነት ተከፍቶ ለአንድ ሣምንት ቆይታ አድርጎ ተጠናቋል፡፡
ከተሞች ካቀረቡት ዓውደ ርዕይ ጎን ለጎን በከተማ ልማት ዘርፍ በተለያዩ ጽንሰ ሃሳቦች ዙሪያ የፓናል ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን በዘርፉ ብዙ ልምድና ዕውቀት ያላቸው የተለያዩ ምሁራን ታድመውበታል፡፡

ላለፉት 6 ቀናት በከተማ ልማት ዘርፍ ስራዎቻቸውን ሲያቀርቡ የነበሩ 124 ከተሞች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው መስፈርት ተወዳድረው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ላገኙ ከተሞች ሽልማት ተሰጥቷል፡፡
በምድብ አንድ ከተካተቱት ከተሞች መካከል አዳማ ከተማ አስተዳደደር የአንደኝነትን ደረጃ ስትጎናጸፍ ሀዋሳና ደሴ ከተማ ሁለተኛና ሶስተኛን ደረጃ አግኝተዋል፡፡
በምድብ ሁለት ከተወዳደሩ ከተሞች ውስጥ ቡታጅራ ከተማ አንደኛ ስትሆን ባሌ ሮቤና ነቀምት ከተማ የሁለተኛና የሶስተኛ ደረጃ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በምድብ ሶስት ከተወዳደሩ ከተሞች ውስጥ ከሚሴ ከተማ አሸናፊ ስትሆን ወራቤና ሊሙ ገነት ከተማ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ በማግኘት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በተጨማሪም በምድብ አራት ከተወዳደሩ ከተሞች መካከል ኮንሶ ካራት ከተማ አሸናፊ ስትሆን ግልገል በለስና እምድብር ከተማ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ በማግኘት ተሸልመዋል፡፡
በመጨረሻም የ9ኛው የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም ልዩ ተሸላሚ የአዲስ አበባ፣ የሸገርና የአዘጋጇ ወላይታ ሶዶ ከተማ ሲሆኑ 10ኛውን የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም እንድታዘጋጅ ሰመራ ከተማ ተመርጣለች፡፡
