እታገኘሁ መኮነን
የካቲት 13/2016
የኢትዮጵያ አብዮት እነሆ ሃምሳ አመት ደፈነ፡፡ በዚህ ሃምሳ ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ለታዩ የፖለቲካ ከፍታና ዝቅታዎች አብዮቱ ምን አበረከተ ? ሲል ለመጠየቅ እና ለማወያየት መዘጋጀቱን ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS) ባሳለፍነው ሰኞ የካቲት 11/2016 ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ አብዮት ‹‹ከየካቲት እስከ የካቲት›› በሚል ርዕስ በስድስት ወሳኝ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር የውይይት መድረክ ከያዝነው የካቲት ወር ማብቂያ ጀምሮ በየሁለት ወሩ ለማካሄድ መዘጋጀታቸውን የተናገሩት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የራስ ወርቅ አድማሴ (ዶር ) ናቸው፡፡የአብዮቱ መሰረታዊ ጥያቄ መልስ አግኝቷል ወይስ አላገኘም ? አገሪቱንስ ወዴት አቅጣጫ ወሰዷት ? የመሬት ለአራሹ አዋጅ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን ጥያቄ መልሷል ወይስ አልመለሰም ?የማንነት ወይም የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ፣የመደብ ትግል እና የሰራተኛ ጉዳይ ፣ የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ የት ደርሷል ? የመጪው ሃምሳ አመት ጉዞስ እንዴት ይታያል? በሚሉ እና በተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ ነው ውይይቱ የሚደረገው፡፡
ያለፈውን ጊዜ አንስቶ ለመወቃቀስ እና ለመወዳደስ ብቻ ሳይሆን ያለፈውን ታሪክ እና መንገድ ዘወር ብለን በሰከነ ምሁራዊ ዕይታ በመፈተሸ የነገ መንገዳችንን ለማበጀት ስንል ይህንን ውይይት አዘጋጅተናል ብለዋል የአዘጋጁ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ አባላት ፡፡ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ይህንን ውይይት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካሉ የተለያዩ ተቋማትና ክፍሎች ጋር በመተባበር እንደሚያዘጋጀውም ተነግሯል፡፡

የ1966ቱ የየካቲት አብዮት በሃገሪቱ ከፍተኛ እና ሥር ነቀል የሆነ ማዕበል በማስነሳት መሰረታዊ የስርዓተ መንግስት ለውጥ ያመጣ አብዮት ነው፡፡ ለውጡ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ ላለችበት አዎንታዊም አሉታዊም ሁኔታ ይህ ነው የማይባል አስተዋጽዖ እንዳለው በርካታ ምሁራን የሚስማሙበት ሃቅ ነው፡፡ሆኖም ይህ አብዮት እና ያስከተለው ውጤት እስከአሁን ድረስ በምሁራን እይታ በጥልቀት አልተጠናም ያሉት የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ የራስ ወርቅ አድማሴ( ዶር) በዚህ የውይይት መድረክ ያለፈውን የሃምሳ ዓመታት ጉዞ በመፈተሸ አሁን ሃገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊ ሁኔታ ለማየት እና ለመገምገም ዕድል ይሰጣል ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በዘመኑ ከነበሩ ምሁራን አንስቶ በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ እና የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ወጣቶች ጭምር እንደሚሳተፉ ተነግሯ፡፡
ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ የተለያዩ ፋይዳ ያላቸውን ወሳኝ ማህበራዊ ጉዳዮች እየመረጠ በዘርፉ ባለሞያዎች በጥልቀት በማስጠናት ለፖሊስ አውጪዎች እና ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ የሚታወቅ 25 ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ ሃገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡
