የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ በ100 ሺ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ወሰነ::

27/06/2016

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ፤ 100 ሺህ ብር የዋስትና ገንዝብ በማስያዝ ጉዳያቸውን በውጭ እንዲከታተሉ በፍርድ ቤት ተወሰነላቸው። “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥረው ላለፉት 13 ቀናት በእስር ላይ የቆዩት አቶ በቴ ዛሬ የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ቀርበው ነበር፡፡

በዛሬው ችሎት ላይ ፖሊስ “ምርመራዬን አልጨረስኩም” በሚል ተጨማሪ 11 የምርመራ ቀናትን ጠይቋል።የአቶ በቴን የስልክ የምርመራ ውጤት ለመቀበል ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በተደጋጋሚ ጥያቄ ባቀርብም   እስካሁን ውጤቱን ለመቀበል አልቻልኩም ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሰው ማስረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልጓቸው አስረድተዋል። 

የአቶ በቴ ጠበቃ  አቶ ቦና ያዘው፤ በተጠርጣሪው ስልክ ላይ “ምርመራ ያደርጋል” የተባለው የመንግስት መስሪያ ቤት በመሆኑ መስሪያ ቤቱ ውጤቱን ያላቀረበበት ምክንያት ለችሎቱ ሊነገር ሲገባው አለመደረጉ፤ ፖሊስ በተሰጡት ቀናት  ምንም እንዳልሰራ ያመለክታል ብለዋል፡፡

ፖሊስ በደንበኛቸው ላይ አራት የወንጀል አይነቶችን በማቀያየር ሲያቀርብ መቆየቱን የተናገሩት ጠበቃው፤ እስካሁን ያለው የምርመራ ሂደት አቶ በቴ ከታሰሩ በኋላ “ወንጀል እየተፈለገባቸው መሆኑን” የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ ህገ መንግስቱን፣ የወንጀል ህጉ እና የወንጀለኛ ህግ ስነ ስርዓትን የሚጣረስ መሆኑን አብራርተዋል። 

በእስር ላይ የሚገኙት ደንበኛቸው “ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚያካሄዱ”እና በዚህም “በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ” መሆናቸውን አቶ ቦና ለችሎቱ አስረድተዋል። የአራት ልጆች አባት እና በአሁኑ ወቅት ህመምተኛ የሆኑት አቶ በቴ፤ በግብርና ስራ የሚተዳደሩ እና ቋሚ አድራሻ ያላቸው መሆናቸውን ጠበቃቸው ጨምረው ገልጸዋል። አቶ በቴ በዋስትና ቢለቀቁ በተፈለጉ ጊዜ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ መሆናቸውን ያስገነዘቡት ጠበቃው፤ በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን እንዲጠበቅላቸው አመልክተዋል። 

በጠበቃው ያልተነሳ ነጥብ ካለ እንዲናገሩ ዕድል የተሰጣቸው አቶ በቴ፤ በራሴ እና በፖለቲካ ፓርቲዬ ላይ “አፈና ነው የተደረገብኝ” ብለዋል። የደህንነት መስሪያ ቤት ገለልተኛ ሊሆን እንደሚገባው የተናገሩት የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር፤ መስሪያ ቤቱ “በእኛ እና በብልጽግና ፓርቲ መካከል ባለው ሰላማዊ ትግል መሃል በመግባት፤ እኔን እና የድርጅቴን እንቅስቃሴ ማፈን አልነበረበትም” ሲሉ ተደምጠዋል። 

እርሳቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተጥሶ እንደሆነ የገለጹት አቶ በቴ፤ የሚዲያ እና የመናገር ነጻነት ሊከበር ይገባ እንደነበርም አጽንኦት ሰጥተዋል። “እስካሁን የተደረገብኝ ግፍ ነው” ያሉት ፖለቲከኛው፤ ፍርድ ቤቱ ይህን ተረድቶ በነጻ እንዲለቅቃቸው ጠይቀዋል። ደንበኛቸውን ተከትለው ተጨማሪ ነጥቦች ለማከል ዕድሉን የወሰዱት ጠበቃ አቶ ቦና፤ ከእርሳቸው ጋር ተይዘው የነበሩት የውጭ ሀገር ዜጋ “ነጻ” ተብለው መለቀቃቸውን ጠቅሰዋል።


ይህንን ተከትሎ ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኛ፤ ፖሊስ በምርመራ መዝገቡ የቀረውን እንዲያስረዳ በድጋሚ ጠይቀዋል። መርማሪ ፖሊስ፤ በአቶ በቴ ላይ ምርመራ እያካሄዱ ያሉት ቀድሞም በተጠረጠሩበት “ሁከት እና ብጥብጥ ማነሳሳት” በሚለው ወንጀል መሆኑን  ገልጸዋል። የስልክ የምርመራ ውጤት ከኢንሳ ለመቀበል የጠየቁት 11 ቀናት እንዲፈቀድላቸውም በድጋሚ ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን አስተያየት ያደመጡት የችሎቱ ዳኛ፤ አቶ በቴ 100 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ በማስያዝ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ውሳኔ ሰጥተዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ፖሊስ መዝገብ አደራጅቶ በፍጥነት ክስ እንዲመሰርት ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

አቶ በቴ በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ “አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ለተሰኘው የዜና ድረ ገጽ ዘጋቢ ከሆነው  አንቷን ጋሊንዶ ጋር ሐሙስ የካቲት 14፤ 2016 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በውይይት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው።