“ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎች የሥነ ልቦና አገልግሎት፣ የሕግና የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እየተደረገላቸው አይደለም፡፡” ኢሰመኮ

የካቲት 13/2016

እታገኘሁ መኮነን

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል አምስት ዞኖች አስተዳደሮች ውሰጥ ሰብዓዊ መብትና ሰብዓዊ ቀውስን በተመለከተ አካሄድኩት ያለውን የምርመራ ሪፖርት ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ በሪፖርቱም በትግራይ ክልል በተለያየ ጊዜ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎች የሥነ ልቦና አገልግሎት፣ የሕግና የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን አስታውቋል፡፡

አብዛኞቹ  ጥቃቶች የተፈጸሙት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ነው ያለው ኮሚሽኑ በተለይ ደግሞ ጥቃቱ ተባብሶ የሚታየው በኤርትራና በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኙ  አካባቢዎች እንደሆነ ተገልጽዋል፡፡ ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ መገለል ስሚደርስባቸው ከማህበረሰቡ እየራቁ እና ለስነልቦና ጉዳት እየተዳረጉም ነው ሲል ኮሚሽኑ የችግሩን ስፋት ትናንት ባወጣው ሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ የቀድሞ ታጣቂዎች መደበኛ ፖሊስንና የማረሚያ ቤት ተቋማትን ሲቀላቀሉ በቂ ሥልጠና ስላልተሰጣቸው፤ በእስር ላይ ባሉ ዜጎች ህይወት ላይ አደጋ ተደቅኗል ብሏል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፡፡ የቀድሞ ታጣቂዎች በማረሚያ ቤት በሚገኙ ታራሚዎች ላይ   ድብደባ፣ ያልተገባ ቅጣት፣ እጃቸው አስሮ ማስቀመጥ ፣ማሰቃየት ሰብዓዊ መብትን ያልጠበቁ አያያዞችና ከሕግ ውጪ የሚደረጉ እስሮችን እየፈጸሙ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ኢሰመኮ በሪፖርቱ የፍትሕና የፀጥታ ተቋማቱ ላይ አፋጣኝ የአቅም ግንባታ በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ መሠረት ያደረገ ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርት በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች በመብዛታቸው የአቅርቦቱ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን፣የክልሉ የጤና ተቋማት መልሰው አገልግሎት ለመስጠት ከደረሰባቸው ውድመት ሙሉ በሙሉ አለመጠገናቸውን፣ በክልሉ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት የደረሰባቸው ውድመትና ዝርፊያ ትምህርትን መልሶ ለማስጀመር አዳጋች መሆኑን ፣ በሰላም የመኖር መብት አደጋ ውስጥ መውደቁን፣ የሕፃናትና የእናቶች ሞት ከሰብዓዊ ቀውስ ጋር መባባሱንና አፋጣኝ ዕርምጃ የሚያስፈልገው መሆኑን አስታውቋል፡፡

ሪፖርቱ በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን በተመለከተ እ.ኤ.አ. በየካቲት 2024 ብቻ 12,000 አዳዲስ ተፈናቃዮች መመዝገባቸውን፣ ከክልሉ ባለሥልጣናት መረጃ ማግኘቱን አመላክቷል፡፡

በአጠቃላይ በክልሉ መጠነ ሰፊ የሆነው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ቀውስ አፋጣኝ ዕርምጃ ይፈልጋል ያለው ኮሚሽኑ ለዚህም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌዴራል መንግሥቱና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተፋጠነ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲኖር እንዲሠሩ ጠይቋል፡፡

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ከክልሉ አደጋ ሥጋት ቢሮ አገኘሁት ባለው መረጃ 6.5 ሚሊዮን ወይም 84 በመቶ የሚሆኑ ወገኖች ዕርዳታ ጠባቂ ናቸው፡፡

በትግራይ ክልል ተፈናቃዮችም ሆኑ ባሉበት ሆነው ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን የሚጠብቁ ዜጎች የሚያገኙት ድጋፍ አነስተኛ ነው ያለው  ኮሚሽኑ፣ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አገኘሁት ባለው መረጃ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ በረሃብና ተያያዥ ሕመሞች ምክንያት አንድ ሺሕ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ አስታውቋል፡፡

በመጠለያዎቹ በረሃብና በተያያዥ ሕመሞች ሕፃናትና እናቶች እንደሚሞቱ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የዕርዳታ አስተባባሪዎች መረጃ ማግኘቱን ገልጿል፡፡ ኮሚሽኑ  በረሃብና ተያያዥ በሽታዎች መሞታቸውን ባያረጋግጥም፣ የተባለው ሞት ሊከሰት እንደሚችል ግን አሳማኝ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡ በርካታ ተፈናቃዮች የሚገኙት በትምህርት ቤቶች በመሆኑ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ትምህርት ቤቶችን ተጠቅሞ ወደ ትምህርት ሥራ ለመግባት አስቸጋሪ እንደሆነበትም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ምልከታ አደረግኩበት ያለው የማይጨው ማረሚያ ቤት በቂ የሰው ኃይል የሌለው በመሆኑ፣ በአንድ መታሰሪያ ክፍል ውስጥ 90 ሰዎች እንደሚገኙ ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ አስር ቤት የሚገኙ ታራሚዎች በቀን ሦስት ጊዜ ምግብ ያገኛሉ ብሏል፡፡ በሽሬ ማረሚያ ቤት የምግብና የውኃ አቅርቦቱ ወቅቱን ያልጠበቀ መሆኑን፣ አቅርቦቱ በማኅበረሰቡና በድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች የመስጠት ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው ተብሏል፡፡

ኮሚሽኑ በኃይል እንዲፈናቀሉ በተደረጉ፣ ከሕግ ውጪ በተገደሉ፣ ፆታዊ ጥቃት በደረሰባቸው ዜጎችና ከሕግ ውጪ ተደረጉ በተባሉ የእስር ወንጀሎች ፈጣንና ሁሉን አቀፍ የሆነ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡