ትናንት በህዝብተወካዮች ም/ቤት የኢትዮጵያን የፀጥታ ሁኔታበሚመለከት ማብራሪያ ያቀረቡት ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የኢትዮጵያን ሰላም የሚያውኩት አካላት የፖለቲካ ፍላጎት የማሳኪያ ልምምድ የሌላቸው ናቸው ሲሉ የተቹ ሲሆን ከሸኔ ጋር በታንዛንያ የተደረገው ድርድር ያለ ውጤት በመጠናቀቁ ምክንያት ምንም ለህዝብ ይፋ ማድረግ የተቻለ ነገር የለም ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የሚታየውን አለመረጋጋት በተመለከተ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ልማት፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እና የወሰን ጉዳዮች ናቸው ያሉ ሲሆን ከሰላም ማስከበር ጋር በተያያዘ ግን መንግሥት በቀጣይነት ሕግ የማስከበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
እጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀመጡ የሚለውን ጉዳይ አንስማማም አንቀበልም አናደርግም። መንግሥት ነን አቅም በፈቀደ መጠን ሕግ ለማስከበር እንሰራለን ሲሉ አክለዋል።
“ሕግ ለማስከበር ስንሰራ በየአንዳንዷ ሰከንድ ለሠላም ዝግጁ የሆነ ኃይል ካለ በራችን ክፍት ነው ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕግ የማስከበሩን ሥራ ከንግግር እና ከውይይት ውጭ እንዲሆን አንፈልግም ብለዋል።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች ጉዳይ ላይ ከመርማሪ ቦርዱ ጋር ውይይቶች መደረጉንም በማንሳት፤ “ሪፖርቶችም ቀርበውላችዋል” ሲሉ ለምክር ቤቱ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእስር ካሉት አብዛኞቹ ወይንም በሺህ የሚቆጠሩት ተምረው ወጥተዋል ያሉ ሲሆን አሁን ላይ በመቶ የሚቆጠሩ ብቻ በእስር ቤት ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።
በእስር ላይ የሚገኙትም “እየተጣሩ፣ እየተማሩ ሊፈቱ ይገባል እንጂ፤ ለደሃ መንግስት እስረኞችን መቀለብ የሚያዋጣ አይደለም” ብለዋል።
“አሁን እንዳለው ስርዓት አልበኝነትና ጥፋት እስር ቢበዛ ኖሮ ፓርክ ሳይሆን እስር ቤት ነበር የምንገነባው። በጣም ብዙ መታሰር የሚገባቸው ሰዎች በየቀኑ ይታለፋሉ” ሲሉም አክለዋል።
ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጋር በተያያዘ መንግስት አምባገነን ቢሆን ኖሮ በሀገሪቱ ይህን ያህል ስርዓት አልበኝነት አይበዛም ነበር’’ ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘’ዲሞክራሲ ከሌለ ይህን ያህል ለህግ አለመገዛት ከየት መጣ?’’ ሲሉ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ‘’ዲሞክራሲ በሌለባቸው ሀገራት ሰዎች በሀገራቸው ብቻ ሳይሆን በሌላም ሀገር ሆነው ትንፍሽ ማለት አይችሉም’’ ብለዋል፡፡ስርዓት አልበኝነት የተበራከተው ዲሞክራሲ መለማመድ፣ ነፃነትን ማስተዳደር ችግር ስለገጠመን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
‘’በደርግ እና በኢህአዴግ ጊዜ ያለ ፍርድቤት ውሳኔ ሰዎች መግደል ነበር እኛ ግን እንኳን መግደል ሰዎችን ማሰር ችግር ሆኖብናል፣ የምናስበው ዲሞክራሲ ስለሆነ ነው’’ ሲሉ አስረድተዋል፡፡

“እስካሁን ባለኝ መረጃ በረሃብ ምክንያት የሚሞት ሰው የለም”
በአሁኑ ሰዓት በብዙ የሃገሪቱ ክልሎች ከፍተኛ ድርቅ መከሰቱን የተለያዩ ሃገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ተቋማት እየተናገሩ ባለበት በዚህ ወቅት ትናንት በህዝብተወካዮች ም/ቤት ስለችግሩ ጥያቄ የቀረበላቸው ዐብይ “እስካሁን ባለኝ መረጃ በረሃብ ምክንያት የሚሞት ሰው የለም” ሲሉ ገልጸው ያለው ችግር በረሃብ ላይ ተጓዳኝ በሽታዎች ተከስተው ያመጡት ነው ብለዋል፤ ወባ ሲጨመር፣ ተቅማጥ ሲጨመር በምግብ እጥረት የተመጣጠነ ምግብ ሲጠፋ እና እላዩ ላይ ሲጨመር መቋቋም አቅቶት ሊሞት ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት በአማራና ትግራይ ክልሎች በድምሩ 372 ሰዎች በምግብ እጥረት ምክንያት መሞታቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርቁ በሚያስከትለው ረሃብ ምክንያት ሞት እንዳይከሰት መንግስታቸው ከረድዔት ተቋማት በላይ ከፍተኛ በጀት መድቦ እንደሰራም አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ትኩረት አልሰጠውም መባሉን የተቹት ጠ/ሚኒስትሩ መንግስት 15 ቢሊየን ብር አውጥቶ ለተረጂዎች እርዳታ ለማዳረስ ጥረት አድርጓል ብለዋል፤ ልማት ቀንሰን ሰው እንዳይሞትብን አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል።አሁንም እናወጣለን ሲሉ ጠቁመዋል።
