ስታንዳርድ ባንክ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት የባንክ ፍቃድ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።

ዋና መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገው ባንኩ  በአፍሪካ ትልቁን ያልተነካ ገበያ እየፈለገ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከሁለት ሳምንት በኃላ ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት የኢንቨስትመንት የባንክ ፍቃድ ማመልከቻዎችን እንደሚቀበል በመግለፁ  ጥሪውን ተቀብሎ ፍቃደኝነቱን አሳይቷል፡፡

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንክ ፍቃድ ለማግኘት ዝቅተኛው የተከፈለ ካፒታል ለዉጪ ባንኮች 100 ሚሊዮን ብር እና ከባንክ ላልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት 25 ሚሊዮን ብር ሀብት ሊኖራቸው ይገባል።

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች የባንክ ፈቃድ ለመስጠት ማቀዷን ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ እንዳሉት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባንኮች እና ባለሀብቶች የባንክ ፈቃድ እንደሚሰጥ ተናግረው ነበር፡፡

እስካሁን የኢትዮጵያ ባንክ ዘርፍ ለውጭ አገራት መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች ዝግ ሆኖ የቆየ ሲሆን፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ግን ለውጭ አገራት ተፎካካሪዎች ክፍት ይደረጋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም የውጭ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፉም ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር በጋራ የሚሰሩበት አማራጭ ሊኖር እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡

የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በባንክ፣ በቴሌኮም፣ በትራንስፖርት እና አቬሽን ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ካሳዩ ቆይተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለውጭ ኢንቨስተሮች ዝግ ተደርገው የቆዩ ዘርፎች ክፍት እንደሚደረጉ ቃል የገቡ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የውጭ ቴሌኮም ፈቃድ ማግኘቱም ይታወቃል፡፡

በተጨማሪም የመንግሥት የልማት ድርጅት እና ብቸኛ የቴሌኮም ድርጅት ሆኖ የቆየውን የኢትዮ ቴሌኮም 45 በመቶ ድርሻ ለውጭ ባለሀብት በመሸጥ ሦስተኛ የውጭ ቴሌኮም ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ቢወጣም ተወዳዳሪ በመጥፋቱ ጨረታው ተሰርዟል፡፡