1 ነጥብ 7 ትሪሊየን ብር በቴሌብር ብቻ ማንቀሳቀስ ተችሏል -ኢትዮ ቴሌኮም

14/06/2016

የቴሌ ብር አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ በአጠቃላይ የግብይት መጠን 1 ነጥብ 7 ትሪልየን ብር በኢኮኖሚው ላይ ማንቀሳቀሱን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።

ኢትዮ ቴሌኮም ይኼን የገለጸው የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ ስራ አፈጻጸሙን በዛሬው ዕለት ጥር 14 2016 በስካይ ላይት ሆቴል ባሳወቀበት መድረክ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ቴሌ ብር አገልግሎት ከ41 ሚሊየን በላይ ደንበኞች ማፍራቱንም ተናግረዋል፡፡እንዲሁም በቴሌብር ሳንዱቅ፣ ቴሌ ብር እንደኪሴ፣ ቴሌብር መላ እና ሌሎችም የፉይናንስ አገልግሎት 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ደንበኞችን አፍርቶ፤ 8 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የብድር አገልግሎት እንዲሁም በቁጠባ አገልግሎት 8 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መቀመጡ ታውቋል።

በተጨማሪም ከዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራዎች ጋር በተያያዘ 602 መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የአገልግሎት ስርዓታቸውን ከቴሌብር ጋር ማስተሳሰራቸውን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞቹ ብዛት 74 ነጥብ 6 ሚሊየን ያደረሰ ሲሆን ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር በ4 ነጥብ 7 ሚሊየን ማለትም 6 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ተገልጿል።