አስፋውን ተሰናበትነው  

በበርካቶች ዘንድ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ “ሞቅ ደመቅ ሸብረቅ” በምትል ንግግሩ ይታወቃል፡፡ አስፋው መሸሻ፡፡ መሸሻ ይሙት የሚለው መሃላውም አይረሳም፡፡

ከአባቱ ከአቶ መሸሻ አስፋው እና ከእናቱ ከ ወ/ሮ ዘነበወርቅ አሻግሬ ሀምሌ 1959 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ‹‹ሰሜን ማዘጋጃ  ችሎት ሰፈር››  በሚባለው አካባቢ የተወለደው አስፋው ለቤተሰቡ አምስተኛ ልጅ እንደሆነ ይነገራል።አባቱ ዲፕሎማት በመሆናቸው እና ለሥራ ጉዳይ ወደ ተለያዩ ክፍለ ዓለማት ይዘዋወሩ ስለነበር ትምህርቱን በኢትዮጵያ፣ታንዛንያ እና ኬንያ ተከታትሏል።

አስፋው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ  ከጓደኛው ዳንኤል ግዛው ጋር በኤፍ ኤም 97.1 ላይ በጋራ  “አይሬ”የተሰኘ ፕሮግራም ማዘጋጀት እና ማቅረብ ጀመረ፡፡ በአይሬ ፕሮግራሙ ተወዳጅነትን ያተረፈው አስፋው ከሃገር እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በኤፍ ኤም 97.1 ራድዮ እና በዛሚ ራድዮ አገልግሏል።

ከሃገር ከወጣም በኋላ “ኑሮ በአሜሪካ” የተሰኘ ትኩረቱን በአሜሪካ በስደት ላይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ህይወትን የሚያስቃኝ ፕሮግራም በ ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ማቅረብ ጀመረ።ከዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሃገር ቤት የተመለሰው አስፋው በተለይም በብዙዎች ዘንድ እውቅናን እና ተወዳጅነት ያስገኘለትን “እሁድን በኢቤኤስ” የተሰኘ ፕሮግራም  አዘጋጅ እና አቅራቢ በመሆን ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ አገልግሏል።

አስፋው መሸሻ በመዝናኛው አለም በጠቅላላ ከ27 አመታት በላይ በኢቢኤስ ደግሞ ለ 14 ዓመታት በመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጅ እና አቅራቢነት አገልግሏል።

አስፋው በስራ ላይ እያለ በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም ባጋጠመው ስትሮክ ምክንያት በኢትዮጵያ ህክምናውን ሲከታተል የነበረ ሲሆን ለተጨማሪ ህክምና ወደ አሜሪካ በመሄድ፣ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግለት የቆየ ቢሆንም በህክምና በተረጋገጠው የጭንቅላት ካንሰር ምክንያት ህይወቱን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል።

ጥር 4 ቀን 2016 ዓም ቅዳሜ ከለሊቱ 9:00 ሰዓት በተወለደ በ 59 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አስፋው መሸሻ በ1999 ዓም በሞት ከተለየችው ባለቤቱ አንድ ልጅ የወለደ ሲሆን የቀብር ስነስርዓቱም በትናንትናው ዕለት በርካታ ወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት በ 9:00 በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።