“በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር የሚያሳየው፣ የሀገሪቱ ሁኔታ ለመገናኛ ብዙሃን አመቺ አለመሆኑን ነው”ሲፒጄ

12/06/2016

ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከአፍሪካ ሃገራት ሶስተኛ ደረጃ መያዟን ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (ሲፒጄ) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል። በአፍሪካ በታሳሪ ጋዜጠኞች ቁጥር ኤርትራ ቀዳሚ ስትሆን ግብፅ ሁለተኛዋ ሃገር ሁናለች፡፡

ሲፒጄ ዓመታዊ ሪፖርቱን ባጠናቀረበት ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ገደማ፤ በመላው ዓለም የታሰሩ ጋዜጠኞች ብዛት 320 እንደነበር ገልጿል።ከእነዚህም መሃል 5ቱ ሴቶች ሲሆኑ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር ድርጅቱ መሰል ሪፖርቶች ማዘጋጀት ከጀመረበት ከ1985 ዓ.ም. ወዲህ በከፍተኛነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ መሆኑንም ጠቁሟል።

በአፍሪካ እስካለፈው ህዳር መጨረሻ ድረስ ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ፤ ቢያንስ 67 የሚሆኑ ጋዜጠኞች “ከስራቸው ጋር በተያይዘ ለእስር መዳረጋቸውን” ሲፒጄ በሪፖርቱ አመልክቷል። ከእነዚህ ጋዜጠኞች ውስጥ አስራ ስድስቱን በማሰር እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኤርትራ ናት። በኤርትራ ከታሰሩት ጋዜጠኞች አብዛኞቹ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በወህኒ ቤት ያሉ መሆናቸውን የጠቀሰው ድርጅቱ፤ በዓለም ላይ ካሉ ጋዜጠኞች “ለረጅም ጊዜ በመታሰር” የሚስተካከላቸው እንደሌለም አብራርቷል። 

ግብጽ 13 ጋዜጠኞችን ወደ ወህኒ በመወርወር ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ፤ ኢትዮጵያ ስምንት ጋዜጠኞችን በማሰር በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የሲፒጄ   ሪፖርት ያሳያል።

ስምንቱ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች የታሰሩት፤ በአማራ ክልል ባሉ አማጽያን እና በፌደራል ኃይሎች መካከል ያለውን ግጭት ከዘገቡ በኋላ መሆኑን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ በሪፖርቱ አመልክቷል።  “በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር የሚያሳየው፣ የሀገሪቱ ሁኔታ ለመገናኛ ብዙሃን አመቺ አለመሆኑን ነው” ሲል ድርጅቱ በዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ አስፍሯል።

ቻይና 44 ጋዜጠኞችን በማሠር ቀዳሚውን ሥፍራ ስትይዝ፣ ማያንማር 43 በማሠር ሁለተኛ፣ቤላሩስ 28 ጋዜጠኞችን በማሠር ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።