”የሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛትን የሚመለከት ማንኛውም ስምምነት የሃገሪቱን መንግስት ይሁንታ ሊያገኝ ይገባል” ኢጋድ

በእታገኘሁ መኮነን

09/05/2016

የቀጠናው ሃገራት እና የቀጠናውን ጉዳይ በትኩረት የሚከታተሉ ሁሉ በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ሐሙስ ጥር 9፤ 2016 በኡጋንዳ ኢንተቤ ከተማ ተካሂዷል፡፡ መሪዎቹ በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ባወጡት መግለጫ ”የሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛትን የሚመለከት ማንኛውም ስምምነት የሀገሪቱን መንግስት ይሁንታ ሊያገኝ ይገባል ”  ብለዋል ፡፡መሪዎቹ ማንኛውም ግንኙነት የሶማሊያን ”ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና የግዛት አንድነት ያከበረ ሊሆን እንደሚገባም” አሳስበዋል።

በጉባኤው ላይ የአስተናጋጇ ሀገር ኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ፣  የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ ፣የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ ኤል-ኬሄራጂን እንዲሁም የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር እና የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አኔት ዌበር ተገኝተዋል፡፡ኢትዮጵያ እና ሱዳን ግን በጉባኤው ሳይሳተፉ ቀርተዋል። መሪዎቹ በመግለጫቸው ለኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት መሻከር  ምክንያት የሆኑ ሰሞነኛ ክስተቶች ”እጅግ አሳስቧና” ብለዋል። ኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ የተገነጠለችው ሶማሌ ላንድ  በአዲስ አበባ የተፈራረሙትን  የወደብ ስምምነት ተከትሎ በርካታ ተቃውሞዎች እና ድጋፎች   በየአቅጣጫው ሲደመጡ ከርመዋል፡፡

የሁለቱን ሃገራት ስምምነት ተከትሎ  ሶማሊያ ቁጣዋን የገለጸች ሲሆን ሃገራዊ አንድነታቸውን ለማስጠበቅ ሁሉንም ዓይነት አማራጮች እንደሚጠቀሙ ፕሬዝዳንቱ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ለኢትዮጵያ አስተላልፈዋል።በዚህ መነሻነትም   ሞቃዲሾ አምባሳደሯን ከኢትዮጵያ አስወጥታለች፡፡ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት የማትሰርዝ ከሆነ ወደጦርነት ለመግባት ዝግጁ መሆኗንም የሃገሪቱ መንግሥት ከፍተኛ አማካሪ አስታውቀዋል።

ሱዳን፣ አሜሪካ፣ቻይና፣የአረብ ሊግ እና ግብፅ ከሶማሊያ ጎን እንደሚቆሙ ያሳወቁ ሲሆን የምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግስታት ድርጅት(ኢጋድ) እና ጅቡቲ ሁለቱ ሃገራት ጉዳዩን በሰከነ መንገድ እንዲያዩት አሳስበዋል።

በወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር  የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ በተጠራው በዛሬው  ልዩ ጉባኤ ላይ  የተሳተፉ የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች ሶማሌላንድ የሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛት መሆኗን በመጥቀስ የሶማሊያ ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና የግዛት አንድነት  ለሚከበርበት ”ጥብቅ መርህ ”ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን፤ ማንኛውም የሚደረጉ ግንኙነቶች እነዚህን መርሆዎች ሊያከብሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። ”በሶማሊያ ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ የሚደረግ ማንኛውም አይነት ስምምነት  የሀገሪቱን መንግስት ይሁንታ ሊያገኝ ይገባል ”ሲሉ  አቋማቸውን ተናግረዋል፡፡ የሶማሊያ መንግስት በውሳኔው መደሰቱን ይፋ አድርጓል፡፡