ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ መግለጫን በጥብቅ እንደምትቃወም የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ተናገሩ፡፡

09/05/2016

የአረብ ሊግ በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተደረሰውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ዓለም አቀፍ ሕግን በግልፅ የጣሰ ነው፤  ስምምነቱ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚፃረር ነው በሚል ተቃውሟል። የአረብ አፍሪካና የዓለም አቀፍ መርሆች ላይ በግልፅ የተሰነዘረ ጥቃት ነውም ብሏል።

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የሊጉ መግለጫ፥ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እና ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ የመግባት ሙከራ ነው ብለውታል፡፡

አክለው  ኢትዮጵያ ከብዙ የአረብ ሀገራት ጋር ጥሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላት ሆኖም የአረብ ሊግ የጥቂቶችን ጥቅም ብቻ እያስከበረ ነው ብለዋል፡፡

የአረብ ሊግ ትናንት በግብጽ ካይሮ ባካሄደው የሚኒስትሮች ልዩ ስብሰባ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተደረሰውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ያላትን ሚና የካደ ሀሳብ ማንጸባረቁ ተናግረዋል።

በትናንቱ  የሚኒስትሮች ልዩ ስብሰባ ላይ  የአረብ ሊግ አባል የሆነችው ግብፅ ኢትዮጵያ በአካባቢው የአለመረጋጋት ምንጭ እየሆነች ነው ማለቷም ተሰምቷል።