09/05/2016
የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ወደ ካምፓላ እና አዲስ አበባ ይጓዛሉ ብሏል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመግለጫው ።
አምባሳደር ሐመር በካምፓላ ፤ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እና በሱዳን ላይ በሚያተኩረው 42ኛው የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።
አምባሳደር ሐመር ከካምፓላ በኋላ ወደ አዲስ አበባ እንደሚያቀኑ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ገልጿል።በኡጋንዳ መዲና ዛሬ የሚካሄደው የኢጋድ ስብሰባ ከያዛቸው ሁለት መወያያ ርዕሶች አንደኛው በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ነው።ኢጋድ ይህን በተመለከተ ውይይት ለማድረግ ስብሰባ መጥራቱን ያወደሰችው አሜሪካ ተወካይዋ አምባሳደር ሐመር ምክክሩን እንዲታደሙ መላኳን አሳውቃለች፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1960 የድንበር ወሰን ስምምነት መሠረት አሜሪካ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ዕውቅና ትሰጣለች ሲል መግለጫው አትቷል፡፡
አምባሳደር ሀመር በተጨማሪም ከአንድ ዓመት በፊት በስምምነት የተቋጨውን የትግራይ ጦርነት ተከትሎ የሚከናወነውን ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ ተሃድሶ እና ማሰናበትን በተመለከተ እንዲሁም ተጎጂዎችን መሠረት ስላደረገው የሽግግር ፍትህ ሂደት ዙሪያ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያወሉ ተብሏል።
ማይክ ሐመር በታህሳስ ወር በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ መወያየታቸው የሚታወስ ሲሆን በውይይታቸውም የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት፣ በመበተንና መልሶ በማቋቋም፣ የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመተግበር እና በሰብዓዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደነበር ይታወሳል ፡፡
አምባሳደር ሐመር በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚስተዋሉ የፖለቲካ እና የጸጥታ ቀውሶችን ለመፍታት ውይይት እንዲደረግም አሳስበዋል።
