09/05/2016
የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት ትናንት ጥር 8/2016 ዓም በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ስላለው ሁኔታ ለመመካከር ስብሰባ አካሂዶ ነበር።
የስብሰባው መርሐ ግብር ቀደም ተብሎ የተያዘ አልነበረም፡፡በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በሶማሊያ እና ኢትዮበሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት ስብሰባውን ማድረግ እንዳስፈለገ ምክርቤቱ ተናግሯል፡፡
የሶማሊያ ባለስልጣናት የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለመጠበቅ ወደ ጦርነት ለመግባት ያላቸውን ቁርጠኝነት ካስታወቁ በኋላ ሶማሊያ በጉዳዩ ላይ ስብሰባ እንዲጠሩ ለአፍሪካ ህብረት እና ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት (UNSC) ጥያቄ መላኳ ተሰምቶ ነበር።
ሁኔታው እየተባባሰ በመምጣቱ ሀገራቱ ወደ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ ከሚለው ስጋት በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች የሚገኙበት የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ (ኤቲ ኤም ኤስ) ን ያዳክማል የሚል ስጋት ተፈጥሯል ። በአካባቢው አልሸባብን ለመቆጣጠር የሰራዊቱ በሶማሊያ መገኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው በሰፊው ይታመናል።
አልሸባብ በበኩሉ በኢትዮጵያዊ እና ሶማሊላንድ መካከል የተደረገውን የመግባቢያ ስምምነት ውድቅ አድርጎ በኢትዮጵያ ላይ ዛቻ አዘል መግለጫ ማውጣቱን “አማኒ አፍሪካ” አስነብቧል።
ከስበሰባው በኋላ የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ባወጣው የአቋም መግለጫ ቀደም ሲል እኤአ ጥር 3/2024 የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሀመት ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን ጨምሮ የሁሉም አባል ሀገራት የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ሊከበር እንደሚገባው አፅንኦት የሰጡበትን መግለጫ እንደሚደግፍ አሳውቋል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያም የሁለትዮሽ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነታቸውን የአፍሪካ ህብረት እና የዓለም አቀፍ ህግ መርሆዎችን ባከበረ መልኩ እንዲመሩ አሳስቧል።
ምክር ቤቱ የውጭ አካላት በሁለቱ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚለውን መርህ እንዲያከብሩ ያሳሰበ ሲሆን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው ያለውን ጠንካራ መልካም ጉርብትና፣ ወዳጅነት እና አብሮነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ተጨማሪ እርምጃዎች እና መግለጫዎች እንዲቆጠቡም አሳስቧል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትርጉም ያለው ውይይት እንዲያደርጉ እና ውጥረቶችን እንዲያረግቡ ጥሪ አቅርቧል።
ምክር ቤቱ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ውይይት እንዲያመቻቹና በየወቅቱ ለምክር ቤቱ መረጃዎችን እንዲያቀርቡ አሳስቧል።
ጉዳዩን በንቃት እንደሚከታተል ያስታወቀው በአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት ለአፍሪካዊ ችግሮች መፍትሄ በመስጠት ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ትርጉም ያለው ውይይት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። በተጨማሪም በኢጋድ አዘጋጅነት በዩጋንዳ ካምፓላ በዛሬው ዕለት የሚካሄደውን ልዩ የመሪዎች ስብሰባ በደስታ እንደተቀበለው ምክርቤቱ ገልጿል።
