ጥር 08/2016
በዛሬው ዕለት የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት የኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ሊመክር እንደሆነ በአፍሪካ ህብረት እና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ጥናት እና ምርምር የሚያደርገው “አማኒ አፍሪካ” አስነብቧል፡፡በስብሰባው ላይ የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች ማብራሪያ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡ ስብሰባውን በንግግር የሚከፍቱት የዚህ ወር የምክር ቤቱ ሊቀመንበር የሆኑት፤ በአፍሪካ ህብረት የጋና አምባሳደር አማ ቱም-አሙሃ ናቸው።
እርሳቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴዎዬ፤ ጉዳዩን በተመለከተ ለምክር ቤቱ ገለጻ እንደሚሰጡ “አማኒ አፍሪካ” አስታውቋል። በአፍሪካ ግጭቶችን የመከላከል እና ከተከሰቱም በኋላ የመቆጣጠርና መፍትሄ የማበጀት ዓላማ ያለው የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት 15 አባል ሀገራት አሉት።
ሀገራት በየሁለት እና ሶስት ዓመት በሚደረግ ምርጫ በሚተካኩበት በዚህ ምክር ቤት ውስጥ፤አሁን የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን በመወከል የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ጅቡቲ፣ ታንዛንያ እና ኡጋንዳ ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶማሌላንድ እና ኢትዮጵያ መሀከል በተፈረመው የወደብ ስምምነት ጉዳይ እየተወዛገቡ የሚገኙት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ አባል ባይሆኑም፤ ተወካዮቻቸው ግን በዛሬው ስብሰባ ላይ ማብራሪያ ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ “አማኒ አፍሪካ” ጠቁሟል። እና ምክር ቤቱም ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንደሚያወጣ ተገልጿል።
አዲስ ጊዜ ቆየት ብሎ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃዎችን ያክልበታል፡፡
