በእናቶችና አረጋውያን ሴቶች ላይ ግርዛት እየተፈጸመ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሃዲያ ዞን በሻሸጎ ፣ ሶሮና ምዕራብ ሶሮ ወረዳዎች በሴቶች ላይ በሚፈጸም ግርዛት ዙሪያ ባከናወነው ክትትል የተለዩ ግኝቶችን ይፋ አድርጓል።

በሻሸጎ ወረዳ በማኅበረሰቡ ዘንድ ‘ጨበላ’ በመባል የሚታወቅ የተደጋጋሚ ግርዛት ጎጂ ልማድ በአካባቢው በበጋ ወራት በሁሉም ዕድሜ ክልል በሚገኙ ሴቶች ላይ በስፋት እንደሚፈጸም እንዲሁም ሴቶችና ሴት ሕፃናት መራቢያ አካላቸው አካባቢ ለሚያጋጥማቸው የጤና እክል እንደመፍትሔ የሚወሰድ መሆኑ ተገልጿል። በዚህ ጎጂ ልማድ የሚያልፉ ሴቶች ከጤና እክል ጀምሮ እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት የሚደርስባቸው መሆኑ በክትትሉ ከተለዩ ግኝቶቹ መካከል መሆኑን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።

ተጎጂዎች ለሚያጋጥማቸው የጤና እክል እየተሰጠ ያለው ድጋፍና ክትትል አጥጋቢ አለመሆን ሴቶች ከዘመናዊ ሕክምና ይልቅ ወደ ጎጂ ልማዳዊ አማራጮች እንዲያዘነብሉ ምክንያት እንደሆናቸውን ተቋሙ አስታዉቋል፡፡

ድርጊቱን ለማስቆም ያልተቻለው  ድርጊቱ በድብቅ መፈጸሙ ፣ ማኅበረሰቡ ሴትን ልጅ የሚገርዙ ግለሰቦችን መደበቁ ፣ በአካባቢው በቂና ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት አለመኖሩ ፣ የሚመለከታቸው የፍትሕና የአስፈጻሚ አካላት ተቀናጅቶ አለመሥራት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ሲቪል ማኅበራት ትኩረት ማነስ ይገኙበታል ብሏል።

በዞኑ የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ተጀምረው የነበሩ የመከላከልና የንቅናቄ ሥራዎች መቀነስ አሁን ለሚስተዋለው የሴት ልጅ ግርዛት ስርጭት መጨመር አስተዋጽዖ ማድረጉን እና  ኢሰመኮ ያከናወነው ክትትል  የጉዳዩን አሳሳቢነት ያመላከተ መሆኑን ተገልጿል።