በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ የአሜሪካ መከላከያ ኃይልና የኢምባሲው የጸጥታ ትብብር ቢሮ ኢትዮጵያ የተቀበሩ ፈንጂዎችንና ያልፈነዱ የመድፍ ጥይቶችን ለማጽዳት እያደረገች ያለውን ዘመቻ ለማገዝ ከኢትዮጵያ ፈንጂ አምካኝ ተቋም ጋር የጋራ ፕሮጀክት መጀመራቸውን አስታውቋል።
ኢምባሲው፣ ኢትዮጵያ ፈንጂዎችን ለማጽዳት የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ፣ ፔንታጎን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በትብብር የሚሠሩ ባለሙያዎችን መላኩን ገልጧል።የቡድኑ አባላት ከአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር የሰብዓዊ ፈንጂ ማምከን ማሰልጠኛ ማዕከል እና ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የጦር መሳሪያ ማስወገድ እና ቅነሳ ፕሮግራም የተውጣጡ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የዳሰሳ ጥናቱን እና ቀጣይ ድጋፎችን በተመለከተም የኤምባሲው ተወካዮች እና የባለሙያዎች ቡድኑ አባላት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኃላፊዎች ጋር ጥር 6፤ 2016 ዓ.ም. መወያየታቸውን ኤምባሲው ገልጿል።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲደረጉ በነበሩ ውጊያዎች የተቀበሩ ፈንጂዎችና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ለሲቪሎች መሞት፣ ለኅብረተሰቡ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴና የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታትና መልሶ ለማዋሃድ በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀናቸውን ኢምባሲው በሰጠው መግለጫ ላይ ገልጧል።
የዘመቻው ዓላማ፣ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ የግብርና ስራቸውን ለማከናወን እንዲችሉ ማገዝ ነው ተብሏል፡፡ ጥናት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በስድስት ወራት ውስጥ የሰው ኃይል ሥልጠናና የቁሳቁሶች አቅርቦት እንደሚጀመር ኢምባሲው ገልጧል።በኢትዮጵያ የአምስት ቀናት ቆይታ የሚኖራቸው የቡድኑ አባላት፤ በትላንቱ ውሏቸው የኢትዮጵያ ፈንጂ አምካኝ ጽህፈት ቤትን ጎብኝተዋል።
