መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት ያቁም!

እናት ፓርቲ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት ያቁም ሲል አሳሰበ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቤተክርስቲያን ክብረ በዓላት የቤተክርስቲያኒቷን ዶግማ፣ ቀኖናና ሥርዓት ጠብቀው እንዳይከወኑ የሚያደርጉ መንግሥታዊ ጫናዎች ተበራክተዋል ያለው ፓርቲው እንዲህ ያለው ተጽዕኖ ካረፈባቸው በዓላት ውስጥ የጥምቀት ክብረ በዓል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው ብሏል። ይህንኑም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት “የጥምቀት በዓል አከባበርን እና ወቅታዊ ጉዳዮችን” መሠረት አድርጎ ጥር ፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም ከተሰጠው መግለጫ ፓርቲያችን ለመረዳት ችሏል ብሏል በመግለጫው።

በዓሉ የአለም ቅርስ እንደመሆኑ የመንግሥት የፀጥታ አካላት በክብረ በዓሉ የሚሳተፉ ምዕመናንና ጎብኚዎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ያለባቸው በመሆኑ ለበዓሉ ስኬታማነት እና ለምዕመናኑ ደህንነት በሚፈለገው መጠን መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲል አክላል።

መንግሥት ሊፈጥር ያሰበውን ጫና አቁሞ ለክብር በዓሉ የሚገባውን አክብሮት በመስጠት ግብር ከፋዩ ሕዝብ የጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለበት። ይህን እውን ከማድረግ አኳያ የአምልኮ ሥርዓቱ ባለቤት ከሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የቱሪዝም ሚኒስቴር በዩኔስኮ የተመዘገበው የጥምቀት ክብረ በዓል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓት ጠብቆ እንዲከናወን የሚጠበቅባቸውን ድርሻ በመወጣት “ነጻ ተቋም” መሆናቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል ሲል አሳስቧል።

ስለሆነም:-

፩. መንግሥት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፲፩ ላይ “መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው” በሚል የተጠቀሰውን ሀሳብ አክብሮ እንዲንቀሳቀስና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከበዓሉ አከባበር ጋር ተያይዞ እያደረገ ያለውን ጫና በማቆም በዓሉ በተገቢው መልኩ እንዲከበር፤

፪. መንግሥት ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ እሴቶችን አክብሮ አገር እንዲመራ፤

፫. በቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና መሥሪያ ቤት እና መንበረ ፓትርያርክ ዙሪያ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የሚደረግ ጥበቃና ፍተሻ መሰል ድርጊት የቤተክርስቲያኒቱን ይሁንታና ፈቃድ እስካላገኘና እንዲሁም የጋራ ስምምነት እስካልተደረስ ድረስ እንዲቆም እንጠይቃለን ብላል።