(ጥር 04 ቀን፣ 2016 ዓ.ም፣ ድሬዳዋ)
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ከከተማና መሰረተ ልማት ሚስቴር ጋር በመተባበር በማዘጋጃቤታዊ ገቢ ሪፎርም፣ በከተማ ፕላን አፈጻጸም፣ በመሬት አስተዳደር፣ ህጋዊ ካዳስተርና ጽዳትና ውበት ላይ ያተኮረ የሁለት ቀን የልምድ ልውውጥ አውደ ጥናት ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ የልምድ ልውውጥ አውደ ጥናት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈንታ ደጀን እንዳሉት ከተሞችን ለነዋሪዎቻቸው ምቹና በዕቅድ የሚመሩ እንዲሁም የነዋሪዎቻቸውን የአኗኗር ዘይቤ የሚቀይሩ ለማድረግ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር አቶ ፈንታ አያይዘው እንደገለጹት ኢትዮጵያ ሃገረ መንግስት ከመሰረቱ ቀደምት ሃገራት መካከል አንዷ እንደመሆኗ መጠን በአህጉራችን አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚዘጋጀውን የአፍሪካ ከተሞች ፎረምን ለመጀመሪያ ጊዜ እንድታሰናዳ መመረጧ ለከተሞቻችን መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ከተሞቻችን በሃገራችን ለ9ኛ ጊዜ በወላይታ ሶዶ በሚካሄደው የከተሞች ፎረም ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑና እያከናወኑ ያሉትን ስራዎች እንዲያስተዋውቁም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በዕለቱም የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ ሃርቢ ቡሃር እዳስታወቁት የከተሞች የልምድ ልውውጥ ዓውደጥናት መድረኮች በከተማ ልማት ዘርፍ ዙሪያ የሚታዩ መልካም አፈጻጸምና ክፍተትን ለመፈተሽ ወሳኝ መሆኑ በመጠቆም በከተሞች መካከል ያለውን ትብብርና ትስስር ለማጠናከር፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችን በጋራ መፍትሄ ለማፈላለግ እንዲሁም ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም አትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የትብብር መድረኩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዱአለም ጤናው በበኩላቸው እንደተናገሩት ትብብር መድረኩ በሃገር ውስጥ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀትና አባል ከተሞችን በመጋበዝ በከተማ ልማትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ከፍ እንዲል፤ እንዲሁም የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር አቅም እንዲገነቡ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ባለፈው ዓመት 25 የሚሆኑ የትብብር መድረኩ አባል ከተማ ከንቲባዎችን በአውሮፓ፣ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በሰሜን አሜሪካና በእስያ ጥናታዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ በመጋበዝ ዓለም አቀፋዊ ልምዶችን እንዲቀስሙ መደረጉን ጨምረው አስታውቀዋል፡፡
ለሁለት ቀን በሚቆየው በዚህ አውደጥናት ላይ ከተለያዩ ከተሞች የመጡ የትብብር መድረኩ አባል ከተማ ከንቲባዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን በርካታ ከተማ ልማት ነክ ተሞክሮዎች እንደሚቀርቡና የድሬዳዋ ከተማ እስተዳደር የልማት ስራዎች እንደሚጎበኙም ታውቋል፡፡

