ቤተክርስቲያን ያም ይሄን አድርጊ፣ ይሄም ይሄን አድርጊ ስላላት እየተጎተተች የተባለችውን አታስተናግድም” ብፁዕ አቡነ አብርሃም

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸው ወቅታዊ የቤተክርስቲያንን ጉዳይ እንዲሁም ከበዓላት እና በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየታዩ ስላሉ ሃሰተኛ ወሬዎች ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ብፁዕነታቸው በመግለጫቸው ፤ በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያኗ የተለያዩ ፈተናዎች እንደገጠሟት የገለጹ ሲሆን ፤ በየግል በተለያዩ አባቶች፣ በተለያዩ መንገዶች በሚሰበኩ ስብከቶች ፣ በሚፈጠሩ ሁኔታዎች ፣ ለምን ? እንዴት ? ዝም አልሽ ቤተክርስቲያን በሚልም ትልቅ ፈተና ላይ ነች ብለዋል።

ብፁዕነታቸው የማይደፈር ሲደፈር አይተናል ፤ ቤተክርስቲያን ስትደፈር ዝም አንልም ያሉ ሲሆን ቤተክርስቲያን በመንግስት እየታመነች አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

ባለፈው የተለያዩ አባቶች በተለያየ መንገድ ተናገሯቸው ስለተባሉት ጉዳዮች ተነስቶ መንግስት ቀየሜታውን ገልጾ ቤተክርስቲያን መልስ እንድትሠጥበት አሳስቧል  ያሉት ብፁዕነታቸው ቤተክርስቲያንም በስፋት፣ በትኩረት ተወያይታበታለች ይሁን እንጂ የብፁዓን ሊቃነጳጳሳት ጉዳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳይ ነው የሚሆነው ፣ ምክንያቱም አንድ ሊቀ ጳጳስ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ስለሆነ፤ ቀርቦ ተጠይቆ አውንታዊ መልስ ሰጥቶ ስህተት ነው ? እውነት ነው ? ብሎ የሚወሰን እንጂ ብግድ ተብሎ በቋሚ ሲኖዶስ ወይም በሌላ የተለያየ መልኩ እንዲህ ነው እንዲያነው ብሎ መናገር ህገ ቤተክርስቲያናችን አትፈቅድም ብለዋል።


ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓለ ጥምቀቱን ለማክበር በመንግሥት ዘንድ ቤተክርስቲያን ይሄን ትበል ፣ አለበለዚያ እንዲህ አይደለም የሚሉ መልዕክቶች ደርሰውናል ያሉት ብጽዕነታቸው አሉ አሉ እየተባሉ ስለተነገሩ ንግግሮች እና ግለሰቦች፣ ጳጳሳት እና ሊቃነጳጳሳት ከሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ታያለች፣ ትመክራለች ታስተምራለች። ህግ አላት በህጓ መሰረት ትገስፃላች። ከዚህ ውጭ ሱሪ በአንገት አውጣ የሚባል ነገር ቤተክርስቲያን አትሸከምም አትቀበለምም ብለዋል።ሁል ጊዜ ቤተክርስቲያን መሞትን ስራዬ ብላው ይዛ ኖራለች ወደፊትም ሞት ከሆነ በሰላም ለመቀበል ዝግጁ ናት።ይሄን ካደረግሽልኝ ይሄን አደርግልሻለሁ የሚል መደራደሪያ የላትም ፣ ሊኖራትም አይችልም። ድርድሯ ሰላምና ሰላም ብቻ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተይይዞ በተለይም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እንደኮበለሉ እና ሃገር ጥለው እንደሄዱ የሚወራው ወሬ ሃሰተኛ መሆኑን ገልጸው  ያለ ስም ስም መስጠት ይሄ ማህበራዊ ሚዲያ በሚባለው ንፋስ ፣ ምንም ጭብጥ በሌለው ሃይማኖታዊውን ሰው ሃይማኖታዊ አይደለም፤ ለቤተክርስቲያን የሚሰራውን ፣ለሀገር የቆመውን ኮበለለ ፣ ከዳ የሚባል ደካማ አስተሳሰብ የቤተክርስቲያን ህልውና አያናጋም ብለዋል።

https://www.youtube.com/watch?v=1k417-1LV1g&pp=ygUOYWJ1bmUgYWJyYWhhbSA%3D

”ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶክተር) ኮብልለው አልሄዱም፣ ኮብላይም አይደሉም ለእውነት እና ለፅድቅ ለቤተክርስቲያናቸው አንገታቸውን ከሚሰጡ አባቶች አንዱ እንጂ የሚሸሹ የሚኮበልሉ ፣ የሚደበቁ የወንጀል ሰው ሊሆኑ አይችሉም አይደሉምም” ብለዋል።

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በቅዱስ ፓትርያርኩ ፍቃድ፣ እንደ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት አውቆት ለአገልግሎት ቤተክርስቲያን ሊባርኩ ታቦታት ይዘው አስፈቅደው ሰሜን አሜሪካ ሄደዋል ይሄ ደግሞ ዛሬ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ነው የሚሄዱት ሐዋርያው አገልግሎታቸውን እንደፈጸሙ ወደሃገራቸው እንደሚመለሱ አስታውቀዋል።

በተለያዩ የመንግስት አካላት በቤተክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ስላለው ጫና “የማይደፈር ሲደፈር አይተናል ፤ ቤተክርስቲያን ስትደፈር ዝም አንልም” ያሉ ሲሆን ከዚህ በፊት ለመንግሥት ችግር ካለ እዚህ ጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ ንገሩን ብለናቸዋል። እኛ እናርማለን፣ እኛው እናስተካክላለን ፣ አላስፈላጊ እርምጃ አትውሰዱ ብለናቸዋል። ትላንት ግን ከቤተክህነት የሚወጣው በሙሉ ይፈተሻል ዛሬም ፣ የሚወጣ መኪና በሙሉ ይፈተሻል ፤ የሚገባው ግን አይፈተሽም። የሚገባውን የኛ ዘበኞች ይፈትሹ ይሆናል፤ የመንግሥት ወታደሮች ግን አይፈትሹም። አንዱ ሌላ ነገር ይዞ ገብቶ ሲወጣ ፈታሹ ሌላ ነገር ይዟል ተብሎ የቤተክርስቲያን ስም እና ክብር ቢዋረድ ማነው ኃላፊው ?ምንድነው የተፈለገው ? ከቤተክርስቲያን ምንድነው የሚወጣው ? መድፍ ነው ? መሳሪያ ነው ? አከፋፋይ ናት ቤተክርስቲያኒቱ ? አትታመንም? ሲሉ ጠይቀዋል። እኛ መሪዎቹ በማናውቀው ፈታሽ በር ላይ ቆሞ መፈተሽ ድፍረት ነው ብለዋል። ቤተክርስቲያኒቱን ህልውናዋን መፈታተን ነው አቅሟንም መፈታተን ተገቢ አይደለም ሲሉ አክለዋል።

መደፋፈሩ በዝቷል ያሉት ብፁዕነታቸው ”መንግስትም ቤተክርስቲያኒቱን ይደፍራል አልፎ ይሄዳል ጠቅላይ ቤተክህነት / ቤተክርስቲያን እንደ ተቋም ደፍራ አላስፈላጊ ነገር ባትደርስም የደረሰችበት ባለፈው ህገወጥ ሲመት ሲፈፀም ተንቀሳቅሳለች ከዚያ ወዲህ ሰላምን ለማስፈን እየጣረች ነው እንደ ግለሰብ በስሜት የሚናገሩ ሰዎች ይኖራሉ። ቤተክርስቲያኒቱን መድፈር አደጋ ነው። ለሃይማኖቱ የማይሞት የለም፣ ከዚህ በፊት ብዙዎች ሞተዋል ፤ ተከባብረን እንኑር ለሰላም እንኑር።” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ኦርቶዶክስ ሃገር ናት ፣ ለሀገር ዋልታ ናት፣ ምሰሶ ናት አምድ ናት ይሄን ታሪክ አይክደውም። ዘመን ቢያስረጃትም ዘመን ቢጥላትም ዘመን ያነሳታል ብለዋል።



ከአላስፈላጊ ጎጠኝነት እና ዘረኝነት እንራቅ የጎጠኝነት ምንጩም ቤተክርስቲያን ሆናለች ከሃይማኖቴ ቋንቋዬ ይበልጣል የሚሉ ሰዎች የተነሱበት ጊዜ ነው ስወለድ ቋንቋዬን ይዤ ነው የተወለድኩት ሃይማኖት በኃላ የመጣ ነው የሚሉ ካህነት የተፈጠሩበት ወቅት ነው ያሉ ሲሆን ይሄን ሁሉ ተሸክመን አጎንብሰን ቤተክርስቲያንን ለማሻገር እየሰራን ነው ምዕመናን ተረዱን ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ከመጪው የጥምቀት በዓል ጋርም ተያይዞ ምዕመናን ሁከት ከሚያመጣ ነገር እራሳችውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል። በጥምቀት በዓላችን እራሳችሁ አስተናጋጅ እራሳችሁ ተስተገናጋጅ ሆናችሁ ደስ በሚያሰኝ ክብርና ሞገስ ፣ የአለባበስ ስርዓት ከማንኛውም የፖለቲካ አመለካከት የራቀ ቤተክርስቲያን ብቻ የምትወከልበት አከባበር እንድታደርጉ ይሁን ብለዋል።ነገር የሚጭሩትን አላስፈላጊ ነገር የሚያደርጉትን በህግ እና ስርዓት ፤ ቤተክርስቲያን ህጓ በሚፈቅደው ፤ መንግሥትም ህጉ በሚፈቅደው እየተናበብን እንስራ ለዚህ በሩ ክፍት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ገዢ ሰላምና ፍቅር ብቻ ነው አመፅ ፣ ኃይል፣ ጉልበት፣ ጦር የተወሰነ ጊዜ ነው የሚገዛው ከተወሰነ ጊዜ በኃላ በራሱ ይወድቃል። ፍቅርን የሚገዛውን ያህል ማንም ገዝቶ አያውቅም ሀገራችን ሰላም ትሁን የሃይማኖት ሰዎች እንደ ሃይማኖት እናስብ ፣ እንደ ሃይማኖት እንናገር፣ አላስፈላጊ ጀግንነትን እንርሳው። አላስፈላጊ ሙገሳንም እንርሳው። ከአላስፈላጊ ሙገሳ አስፈላጊ በሆነ ወቀሳና ለመጨረሻው መከራ እራሳችንን እናዘጋጅ ብለዋል በመግለጫቸው።

ብፁዕነታቸው ፤ ” አሁን ግራ የሚያጋባው ትላንት ለበዓለ ጥምቀቱ የተሰየመው አብይ ኮሚቴ ከከተማ አስተዳደሩ፣  ከሚመለከታቸው የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር ፣ከታላላቅ ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። በውይይቱ ይህ ከባድ ፈተና እየተነሳ እንዳለና አሁንም በዓለ ጥምቀቱን ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ቤተክርስቲያኒቱ እንዲህ አይነቱን ለይታ እንድታወግዝ ፣ የራሷን መልዕክት እንድታስተላልፍ በመንግሥት አቋም ተይዞ ለአብይ ኮሚቴው ተነግሯል ” ብለዋል።

ቤተክርስቲያን ያራሷ ነፃነት አላት ፣ የራሷ ክብር አላት ፣ የራሷ ነፃ መድረክ ፈላጊ ናት ሁሉም እየተነሳ ያም ይሄን አድርጊ፣ ይሄም ይሄን አድርጊ ስላላት እየተጎተተች የተባለችውን አታስተናግድም ሲሉ ገልጸዋል።

ክፉውን ክፉ፣ በጎውን በጎ፣ መልካሙን መልካም ፤ መልካም ያልሆነውን መልካም አይደለም ብላ ለማስተላለፍ የራሷ ህግ ስርዓት አላት ብለዋል።

” የፈለገ የሚያዛት ፣ የፈለገ የሚያሽከረክራት ፣ ያልወደደ እንደ ወደደ ፍላጎቱን ምኞቱን እንድትፈፅምለት የሚጎትታት ቤተክርስቲያንን ኖራም አታውቅም ወደፊትም ልትኖር አይገባም ” ሲሉ ተናግረዋል።