ሂውማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያውን ስምምነት አላከበረችም ሲል ተቸ።

ሂውማን ራይትስ ዎች አዲስ ባወጣው የዓለም የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ የፕሪቶሪያውን ስምምነት እና የአማራ ክልል ግጭትን የዳሰሰ ሲሆን

በኢትዮጵያ የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ተጠያቂነት እንዲሰፍንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ ወደሚያስችሉ ዓለማቀፋዊ ርምጃዎች አላመራም በማለት ተችቷል።

በአማራና ትግራይ ክልሎች በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና ሌሎች ጥሰቶች እስከአሁንም ቀጥለዋል ያለው ድርጅቱ፣ አውሮፓ ኅብረትና ሌሎች ምዕራባዊያን አገራት ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ግንኙነታቸውን እንደገና ጀምረዋል በማለት ወቅሷል።

የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይደርስ እንደሚያደናቅፉና በአማራ ክልልም ውጊያ፣ የቴሌኮምንኬሽን መቋረጥና በረድዔት ሠራተኞች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ለዕርዳታ ሥርጭት እንቅፋት እንደሆኑ ሪፖርቱ ጠቅሷል።

በሚያዝያ ወር የአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ እየተባባሰ የመጣው  የፌደራል መንግስት የክልሉን የፖሊስ ሃይል ከፌደራል ወታደራዊ ሃይል ጋር ለማዋሃድ መወሰኑን ተከትሎ  ነው ያለው ሪፓርቱ ሚያዚያ 9፣ ሁለት የካቶሊክ የእርዳታ አገልግሎት አባላት በጥይት ተመተው መገደላቸውን ሪፖርቱ ገልጿል።

በነሃሴ እና መስከረም ወር በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞችና ከባድ ጦርነት ተካሂዶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናትናትና ስደተኞችን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋቱና መቁሰሉ እንዲሁም በሲቪል ንብረት እና እንደ ሆስፒታሎች ባሉ መሰረተ ልማቶች ላይ ውድመት ደርሷል ብሏል።

ነሐሴ 23 የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር (OHCHR) እንዳረጋገጠው ከሆነ ከሰኔ እስከ ነሐሴ በተካሄደው ጦርነት ቢያንስ 183 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጧል። በአማራ ክልል የቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎችም ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ሪፓርቱ ገልጿል።