ከአባላት መታሰርና የጽህፈት ቤት መዘጋት ጋር በተያያዘ ክስ የሚያቀርበው የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ በሰላማዊ የድርድር ማእቀፍ ውስጥ ከገዢው ፓርቲ ብልጽግና ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን ገለጸ፡፡
ኦፌኮን ጨምሮ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ መጻኢ እድል ላይ የሚያካሂዱት የተበጣጠሰ የሰላማዊ ትግል አካሄድ አገሪቱን ከማዳን ይልቅ ወደባሰ አዘቅት እየከተታት ነው ያሉት የኦፌኮ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ሁሉን አቀፍ በሆኑ የውይይትና የድርድር ማእቀፍ ውስጥ መወያየት ለአገር የሚበጅ ነው ብለዋል፡፡
ኦፌኮ ላለፉት ዓመታት በሰላዊ የትግል መስመር የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያደርግ የነበረና አሁንም እያደረገ ነው ያሉት ሃላፊው ነገር ግን ለብቻ በሚደረጉ ትግሎች ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ፓርቲው ግንዛቤን ወስዷል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ለኢትዮጲያ የሚበጁ የውይይት ነጥቦች ላይ ለመወያየት በሬ ክፍት ነው ያለው ፓርቲው ለዚህም በተለያዩ የፖለቲካ ስብስቦች ውስጥ በመሆን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ንግግር እያደረኩ ነው ብሏል፡፡
