01/05/2016
ከኢትዮጵያ ጋር የወደብ ኪራይ ስምምነት ውል የገባችው ሶማሊላንድ ስምምነቱን በሚቃወሙ ሰዎች በሶማሊኛ ቋንቋ “ኢትዮጵያዊ ላይ በተገኘበት እርምጃ ይወሰድበት” የሚል በራሪ ጽሑፍ በሐርጌሳ ከተማ እየተበተነ መሆኑ ተነግሯል።
በዚህም ምክንያት በሶማሊላንድ ለሚገኙ ከ 40 ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በጣም አሳሳቢ ወቅት ሆኗል።
በተለይም የኦሮሞ ተወላጆች በሚኖሩበት አካባቢ ላይ ትኩረት በማድረግ በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ለማድረስ፣ ንብረት ለመዝረፍ፣ እና ቤታቸውን በእሳት ለማቃጠል ሙከራ ተደርጓል ተብሏል።
በሶማሊላንድ ሁለተኛ ትልቋ ከተማ በሆነችው በቦርኦ ከተማ በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ጉዳት መድረሱን እና ንብረታቸው መዘረፉ ተነግሯል።
በሶማሊላንድ የስደተኞች ተወካይ እንደሚሉት ስደተኛ ነዋሪዎች ስጋታቸውን ለሶማሊላንድ ባለስልጣናት ካሳወቁ በኋላ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በስፋት በሚገኙባቸው መንደሮች የፖሊስ ኃይል ተሰማርቶ ነበር።
በቦርኦ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሰልፍ ከወጡ በኋላ “የኦሮሞ ተወላጅ ቤቶችን ዒላማ በማድረግ ንብረታቸውን ዘርፈዋል። ከዚህ በተጨማሪም የ70 ዓመት እና የአምስት ዓመት ታዳጊ ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል” ብለዋል።
እርሳቸው በሚኖሩባት የሶማሊላንድ መዲና ሐርጌሳ እንዲሁ በተፈጸም ጥቃት አንድ የ12 ዓመት ታዳጊ ጉዳት ደርሶበት በሆስፒታል እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በሶማሊያ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውን ስደተኞች ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የስምምነቱን መፈረም ተከትሎ በተለይ በመዲናዋ ሞቃዲሹ በርካታ የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን እና በከተማዋ ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ ስሜቶች እየበዙ መሆኑን መኖሪያቸውን በሞቃዲሹ ያደረጉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።
