ከመፅፍቱ ጋር የተቀበረው ወጣት

አሸናፊ አሰበ

01/05/2016

በ 1926 ዓም የየተገነባው  በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ አካባቢ የሚገኘው በተለምዶ ሎምባርዲያ ተብሎ የሚጠራው ህንጻ መጽሐፍን ከነ መጽሐፍ አዟሪው በዕለተ አርብ ታህሳስ 26/2026 ከምሽቱ 1 ሰዓት  ወደ ፍርስራሽነት ተቐይሯል።

ጌትነት ክፍሌ ይባላል መጽሐፍትን እያዞረ በመሸጥ የሚተዳደር ለፍቶ አዳሪ የአንድ ሴት ልጅ አባት ነው። ጌትነት ሎምባርዲያን በአካባቢው ተመሳሳይ ስራ በመስራት ከሚተዳደሩ መጻህፍት ሻጮች ጋር ለመጻህፍት ማሳደሪያነት በኪራይ ይገለገሉበት ነበር።

ታዲያ በተጠቀሰው ቀን  ሎምባርዲያን ለማፍረስ የተንቀሳቀሰ አፍራሽ ግብረ ኃይል በምሽት መጣ ፡፡ጌትነት እና ሌሎች እቃዎቻቸውን እና በውስጥ የነበሩ መጽሐፍቶችን ለማውጣት ወደ መጋዘኑ ገቡ ፡፡ አፍራሽ ግብረ ሃይሎቹግን እነ ጌትነት እስኪወጡ  አልታገሱትም በላያቸው ላይ ማፍረስ ጀመሩ፡፡ የድንጋይ ክምርም ተናደባቸው ፤ጌትነትን ጨምሮ 4 ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ።

ህንፃውን  በላዩ ላይ የናዱበት ጌትነት የጀርባው አጥንት ላይ በደረሰበት ከባድ ጉዳት ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተላከ፡፡ የደረሰበት ጉዳት ከባድ በመሆኑ ሊተርፍ አልቻለም:: ጌትነት አረፈ፡፡ ከመፅሀፍቱ ጋር ተቀበረ፡፡

የሼክ አህመድ ሳለህ አልዛህሪ ህንፃ እንደሆነ የሚነገርለት፥ ሎምባርዲያን ጨምሮ በርካታ አግልግሎት መስጫ ተቋማትን የያዘው ይህ ቅርስ፥ በባለሞያዎች ተጠንቶ በቅርስነት እንዲመዘገብ የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ጥበቃ እንዲደረግለት በ2016 ዓ.ም ማስታወቁን ከዚህ ቀደም ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቦ ነበር።

 ቢሮው ታህሳስ 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ለአዲስ አበባና ዙርያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ልማት ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ፣ ሕንፃው ቅርስ መሆኑን ገልጾ በማስተር ፕላኑ በቅርስነት እንዲያዝ አስታውቆም ነበር፡፡

በወቅቱ ይሄን ጉዳዩ የተከታተሉት ከፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከቅርስ ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክቶሬትና  ከቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት፣ እንዲሁም ከራሱ ከቢሮ የተውጣጡት ባለሙያዎች የቅርስነትን  መሥፈርት ያሟላል በማለት ወስነው ነበር። የማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤቱ ሕንፃውን በቅርስነት እንዲይዘውም ተጠይቆ ነበር፡፡

ሆኖም ከወራት በኋላ የከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውሳኔውን በመሻር፣ ‘ይህ ጥንታዊ ሕንፃ ቅርስ አይደለም’ በማለት አስደንጋጭ መረጃን አውጥቷል።

እንደምክንያት የጠቀሰውም “በከተማችን እየተካሄደ ያለው ልማት መደናቀፍ የሌለበት በመሆኑ በመግለጽ ሕንፃው የቅርስነት መስፈርት አያሟላም” ሲል ውሳኔውን በውሳኔ ሽሯል። በቅርስነትም እንዳይመዘገብ መወሰኑ ታውቆ፥ “እየተዘጋጀ ባለው ማስተር ፕላን ላይ በቅርስነት እንዳይመዘገብ” በማለትም ግልጽ ደብዳቤ ጽፎ ነበር።

ይህ ውሳኔ ተግባራዊ ሆኖ ሎምባርዲያ ካፌን ጨምሮ ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ሱቆች የነበረበት ህንጻ አርብ ዕለት ፈርሷል።