አሸናፊ አሰበ
16/04/2016
በዋግ-ህምራ ብሔረሰብ ዞን የ2015 የክረምት ወቅት የዝናብ ስርጭት መዛባቱን ተከትሎ የተፈጠረው ድርቅ በተለይም በእንስሳት በኩል ተባብሶ መቀጠሉን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ምህረት መላኩ ለአዲስ ጊዜ ተናግረዋል።
በዞኑ ከሚገኙት 9 የገጠር ወረዳ እና 3 የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በተለይም በሦስት ቀበሌዎች የ 2015/16 የምርት ዘመን ሙሉ በሙሉ የተቋረጠ ሲሆን በ 3 ወረዳዎች እና በ26 ቀበሌዎች ውስጥ የከፋ ድርቅ ተከስቷል ብለዋል።
ከ 171ሺ በላይ እንስሳት ወደ ምስራቅ በለሳ እና ሌሎች የሰሜን ጎንደር ዞን አካባቢዎች እንዲሻገሩ ተደርጓል ያሉት ሃላፊው እስከ ታህሳስ ወር ባለው መረጃ 10ሺ በላይ እንስሳት ለሞት መዳረጋቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
በመኸር ወቅት የሰብል ግምገማ መሰረት በድርቁ በቀጥታ የተጎዱ 180,580 ነዋሪዎች እና ተጋላጭ የሆኑ 425,136 ሰዎች የተለዩ ሲሆን ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች በተገኘ 20ሺ ኩንታል እህል እና 240 ሚሊየን ብር ድጋፍ በድርቁ በቀጥታ የተጎዱ ብለን ከለየናቸው ውስጥ እስከ ያለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ አንድ ዙር ድጋፍ ለ112ሺ ሰዎችን አዳርሰናል ብለዋል።
በሰው በኩል በሚደረገው ድጋፍ የተሻለ መረባረብ ቢታይም አንድ ዙር ድጋፍ እንኳ ያልደረሳቸው ከ 67 ሺ በላይ ሰዎች መኖራቸውን ሃላፊው አክለዋል።
ችግሩ ተባብሶ መቀጥሉን እና በዞኑ የሚገኙ በርካታ ምንጮች እየደረቁ በመሆኑ ድርቁ እጅግ እየሰፋ መሆኑን እና የዜጎች ፣የረጂ ድርጅቶች እና የመንግስትን ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን አቶ ምህረት መላኩ ለአዲስ ጊዜ ተናግረዋል።
