“…..በወልቂጤ ተከስቶ በነበረው ሁከት ማጣራት በማድረግ ተጎጂዎች ሊካሱ ይገባል።” ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

16/04/2016

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጉራጌ ዞን እና በቀቤና ልዩ ወረዳ መካከል የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ ባወጣው ሪፖርት እንዳስነበበው ከጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስና ያስከተለውን ጉዳት ከአካባቢው ነዋሪዎች በቀረበለት አቤቱታ መነሻነት ከጥቅምት 20 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በቦታው በመገኘት ምርመራ ማከናወኑን ገልጿል።

ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች እና ምስክሮች ጋር 22 ቃለ-መጠይቆች አድርጓል ያለው ሪፖርቱ ከጉራጌ ዞን፣ ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር እና ከቀቤና ልዩ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን ገልጿል።

ዘረፋ እና ውድመት የደረሰባቸው እና የግል እና የመንግሥት ተቋማትን ኮሚሽኑ ተዘዋውሮ የጎበኘ ሲሆን ተጎጂዎች ሕክምና ካገኙባቸው የሕክምና ተቋማት የሕክምና ማስረጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አሰባስቧል ብሏል።

በጉራጌ እና በቀቤና ማኅበረሰብ መካከል ከዚህ በፊትም የተለያየ መጠን ያለው ግጭት እና የሰላም ስምምነት ጥረት እንደነበር ዘገባው ገልጾ በተለይ ከቀቤና የልዩ ወረዳነት ምሥረታ ጋር በተያያዘ እና የልዩ ወረዳው መቀመጫን በተመለከተ በሁለቱ ማኅበረሰቦች አስተዳደሮች መካከል አለመግባባቱ እየተካረረና የግጭት አደጋው እየጨመረ መምጣቱን አክሏል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች አሁንም ዘላቂ መፍትሔ ያልተሰጣቸው የመዋቅር እና የአስተዳደር ጥያቄዎች ለሰላም እና ደኅንነት እጦት እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት ሆነው መቀጠላቸው እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ፤ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ኃላፊዎች ቅሬታና ጥያቄ የቀረበባቸውን አካባቢዎች ሁሉ ተዓማኒ በሆነና ተቀባይነት ባለው ሂደት በማሳተፍ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመቻቹ ይገባል ብለዋል፡፡

ኮሚሽነሩ አክለውም “በወልቂጤ ከተማ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከሰተው ሁከት እና የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት በመቀናጀትና ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና ተጎጂዎች ሊካሱ ይገባል” ብለዋል፡